የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒቲ ት/ቤት የ2015 ዓ/ም አንደኛ መንፈቀ ዓመት የወላጅ ጉባኤ መጋቢት 02/2015 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የት/ቤቱ አስተዳር ቦርድ አባል አቶ ገዳሙ ጌታቸው በመክፈቻ ንግግራቸው ትምህርት ለሀገር የሚጠቅም ትውልድ የሚኮተኮትበት መሣሪያ መሆኑን ተናግረው ወላጆች፣ መምህራንና ባለድርሻ አካላት በየጊዜው አፈጻጸሙን ማየታቸውና  መመካከራቸው ውጤታማ ለመሆን ይረዳል ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒቲ 2 ደረጃ ት/ቤት ር/መምህር አቶ ካሣሁን ዲጤ እንደገለጹት የትምህርት ሥራ ተማሪዎችን፣ ወላጆችን፣ ፖሊሲ አውጪዎችንና ማኅበረሰቡን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚያሳትፍ በመሆኑ የሚገኘው ውጤት በሀገር ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ይፈጥራል ብለዋል፡፡ ጥራት ያለው ትምህርትን ለተማሪው በማቅረብ በመልካም ሥነ ምግባር የታነጹ፣ በራስ መተማመናቸው የዳበረ፣ ቴክኖሎጂን የሚጠቀሙ፣ ለራሳቸውና ለሀገራቸው ብልጽግና የሚተጉና በሁለንተናዊ መልኩ የዘመኑን ችግር ፈቺ የሆኑዊ ዜጎችን መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ር/መምህሩ ገልጸዋል፡፡ አቶ ካሣሁን የአንደኛ መንፈቀ ዓመት የሥራ ሪፖርት ሲቀርብ በሥራው ያገኘናቸውን ልምዶች በተሻለ ሁኔታ ለማስቀጠልና የሚሻሻሉ ጉዳዮችን ለማሻሻል ከውይይቱ የሚገኙ ጠቃሚ ሃሳቦችን መቀበል እንዲሁም በሚቀጥለው ጊዜ ተማሪዎቻችንን በክፍልም ሆነ በሀገር አቀፍ ፈተና ውጤታማ ለማድረግ መረባረብ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒቲ ሙሉ 1 ደረጃ ት/ቤት ር/መምህር አቶ ምሕረቱ ሚልክያስ በበኩላቸው ትምህርት የሁሉንም ርብርቦሽና የነቃ ተሳትፎ የሚጠይቅ ስለሆነ መንግሥት ከየትኛውም ጊዜ በላይ ትኩረት በመስጠት የፈተና ሥርዓትን በመቀየር፣ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ቤቶችን በመጨመር፣ የውጭ ትምህርት ዕድሎችን በማስፋትና የተማሪዎችን የመማር ፍላጎት በማሳደግ አስፈላጊውን ሥራ እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒቲ ዐጸደ ሕፃናት ት/ቤት ር/መምህርት ወ/ሪት ሣራ ጎይዳ ለሕፃናት ሁለንተናዊ ሰብእና የቅድመ መደበኛ ትምህርት መሠረት የሚጥል መሆኑን ተናግረው የቅድመ መደበኛ ትምህርት ሕፃናት መሠረታዊ ልምዶችን እንዲቀስሙ እንዲሁም ጤናማ ባህርይ ያላቸው፣ ተመራማሪና ንቁ ዜጋ እንዲሆኑ ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ መጨረሻ በቀረበው የ2015 ዓ/ም የአንደኛ መንፈቀ ዓመት ሪፖርት ዙሪያ ከተማሪ ወላጆች ጋር ውይይት የተካሄደ ሲሆን በየክፍላቸው ከ1 - 3 ደረጃ ለወጡ ተማሪዎች የምስክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት