የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የማኅበረሰብ ጉድ/ማስ/ጽ/ቤት በሸክላ ሥራና በእንጨት ለቀማ የሚተዳደሩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ገቢ በማሳደግ አኗኗር ማሻሻል የሚያስችሉ ሁለት ግራንድ ፕሮጀክቶችን ባለድርሻ አካላት በተገኙበት መጋቢት 8/2015 ዓ/ም በይፋ ሥራ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር አካሂዷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ በኃይሉ መርደኪዮስ እንደተናገሩት ምርምሮችና የማኅበረሰብ ጉድኝት ተግባራት በተጨባጭ የማኅበረሰቡን ችግር ሊፈቱ ይገባል፡፡ ሀገር በቀል ዕውቀቶችን በማበልጸግና በምርምር በማጎልበት ማኅበረሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን በማድረግ የሀገር ልማትን መደገፍ እንዲቻል እንዲሁም የደን ጭፍጨፋን ለማስቀረት አማራጭ ገቢንና የገበያ ትስስር መፍጠር ወሳኝ በመሆኑ በሸክላ ሠሪዎች ላይ የሚስተዋለውን መገለልና አድልዖ ለማስቀረት የሃይማኖት አባቶችና አስተዳዳሪዎች በቅንጅት ሊሠሩ ይገባል፡፡

የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው ዳይሬክቶሬታቸው በርካታ የማኅበረሰቡን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመው በሁለቱ ፕሮጀክቶች የተገለጹ ተግባራትን በአግባቡ ወደ ተግባር መቀየር ከተቻለ የፕሮጀክቶቹ ተጠቃሚ የሚሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ገቢ የሚያሳድጉና አኗኗር የሚለውጡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር መስፍን መንዛ ፕሮጀክቶቹ በዋናነት የማኅበረሰቡን የኢኮኖሚ ሁኔታ በማሻሻል ተያያዥ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚረዱ ናቸው ብለዋል፡፡ ኮሌጃቸው በቀጣይም መሰል ፕሮጀክቶችን እየቀረጸና በሚመለከታቸው አካላት እያስገመገመ ተግባራዊ እንደሚያደርግ ዲኑ ጠቁመዋል፡፡

የ“SNV/RAYEE” ፕሮጀክት አርባ ምንጭ ክላስተር ማስ/ጽ/ቤት የወጣቶች ሥራ ፈጠራ አማካሪ አቶ አብነት ጴጥሮስ በዩኒቨርሲቲው የተቀረጹት ሁለቱ ፕሮጀክቶች በሴቶች ላይ ልዩ ትኩረት አድርገው የሚሠሩ በመሆናቸው ፕሮጀክታቸው የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ጠቁመዋል፡፡ በዞኑ ደረጃ ያሉ ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ለማሳደግና የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሌሎችም ፕሮጀክቶች በዩኒቨርሲቲው ተቀርጸው ቢቀርቡ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም አቶ አብነት ጠቁመዋል፡፡

የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የማኅ/ጉድ/ማስ/ጽ/ቤ/አስተባባሪ ወ/ሮ አስቴር ሰይፉ በእንጨት ለቀማ ሥራ የሚተዳደሩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን አኗኗር ለማሻሻል የተዘጋጀውን ፕሮጀክት ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ አማራጭ የገቢ ምንጭን የመፍጠር፣ ጥብቅ ደኖችን የመታደግ፣ በሴቶች ላይ የሚስተዋለውን የሥራ ጫናና ጾታዊ ጥቃት የመቀነስ ዓለማ ሰንቆ የተዘጋጀ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ 150 በእንጨት ለቀማ የሚተደዳሩ ሴቶችን በዘመናዊ የጥጥ ፈተላ ሥራ ላይ በማሠማራት ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን ምቹ የሥራ ቦታና የገበያ ትስስር መፍጠርና ሥልጠናዎችን መስጠት ላይ በትኩረት ይሠራል ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ሁለት ሚሊየን አንድ መቶ ሃያ ሺህ  ብር በጀት የተያዘለት ሲሆን 1.4 ሚሊየን ብር በዩኒቨርሲቲው ቀሪው በ“SNV/RAYEE” ፕሮጀክት የሚሸፈንና ለሁለት ዓመታት የሚቆይ እንደሆነም ወ/ሮ አስቴር ጠቁመዋዋል፡፡

የሸክላ ሥራን ማዘመን ላይ በማተኮር የሚሠራውን የፕሮጀክት ሃሳብ ያቀረቡት  ረ/ፕ ስለሺ አበበ ፕሮጀክቱ የማኅበረሰቡን ጥያቄ መነሻ በማድረግ የተዘጋጀ ሲሆን ምቹ የሥራ ቦታና የገበያ ትስስር መፍጠርና ሌሎች ሥራውን የሚያዘምኑ በርካታ ተግባራት ማከናወን የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ ነው ብለዋል፡፡ ሸክላ ሥራ ከአፈር አቅርቦት ጀምሮ በዘርፉ በርካታ ተግዳሮቶች ያሉበት መሆኑን የገለጹት ረ/ፕ ስለሺ በፕሮጀክቱ በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ  በደጋ ኦቾሎና ጨንጌ ቀበሌያት ላይ በሸክላ ሥራ ላይ የተሠማሩ 100 ሰዎች የሸክላ አሠራራቸውን በማዘመን የገቢ መጠናቸው እንዲያድግና አኗኗራቸው እንዲሻሻል ትኩረት ተደርጎ  እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡  ፕሮጀክቱ ለሁለት ዓመታት የሚቆይና ሁለት ሚሊየን ብር በጀት የተያዘለት እንደሆነም አቅራቢው ጠቁመዋል፡፡  

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ተወካይና አማካሪ አቶ በርገና በቀለ በመዝጊያ ንግግራቸው ሁለቱም ፕሮጀክቶች ማኅበረሰቡን ከችግር የሚያወጡና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ ለፕሮጀክቶቹ ስኬታማነት የዞኑ አስተዳደር የሚጠበቅበትን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አቶ በርገና አረጋግጠዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት