Print

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በራስ ገዝ (Autonomous) አስተዳደር ራሱን ለማስተዳደር እያከናወነ ባለው እንቅስቃሴና ተቋሙ በሚገኝበት አሁናዊ ደረጃ ዙሪያ ከፍተኛ የትምህርት ሚኒስቴር አመራሮች በተገኙበት ከዩኒቨርሲቲው የካውንስል አባላት ጋር መጋቢት 8/2015 ዓ/ም ውይይት ተካሂዷል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከ2011 ዓ/ም ጀምሮ በአዲሱ ፍኖተ ካርታ መሠረት ዩኒቨርሲቲውን ወደ ራስ ገዝ አስተዳደር ለመቀየር ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ የዕለቱ ውይይትም ዩኒቨርሲቲውን ወደ ራስ ገዝ አስተዳደር ለማምጣት በዕቅድ ተይዘው እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ያሉበትን ደረጃ ለካውንስሉና ለትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች በማሳወቅ የማሻሻያ ግብአቶችን ማሰባሳብ እንደሆነ ፕሬዝደንቱ ጠቁመዋል፡፡

ለውይይቱ መነሻ የሚሆኑና ዩኒቨርሲቲው ወደ ራስ ገዝ አስተዳደር ለመሸጋገር ከተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች አንጻር ያከናወናቸውን ተግባራት የተመለከቱ ሁለት ሠነዶች በአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞና በምር/ማኅ/ጉድ/ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ እንዲሁም በቅድመ ዝግጅት ወቅት ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን የተመለከተ ሠነድ በትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ ቀርበዋል፡፡

በቀረቡት ሠነዶች እንደተመለከተው መደበኛውን የመማር ማስተማር ሥራ ከድኅረ ምረቃ ትምህርት ጋር አስተሳስሮ እንዲሄድ የማድረግ፣ በ2ኛና 3ኛ ዲግሪ የተማረውን የሰው ኃይል 50፡50 የማድረስ፣ የምርምር ላቦራቶሪና የተማሪዎች መኖሪያ ለ2ኛና 3ኛ ዲግሪ ተማሪዎች ታሳቢ በማድረግ የማሳደስ፣ ለ2015 የመውጫ ፈተና ዝግጅት የማድረግ፣ የምርምር ዩኒቨርሲቲን ታሳቢ ያደረገ መዋቅራዊ ማሻሻያ የማድረግ፣ የተቋሙን ከባቢያዊና ውስጣዊ ጥንካሬን መሠረት ያደረገ የተቋሙን የትኩረት መስክ ልየታ የማካሄድ ተግባራት መከናወናቸው ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው የገቢ ማስገኛ አማራጮች ላይ ትኩረት በማድረግ የዶሮና እንስሳት እርባታዎችን የማስጀመር፣ በዩኒቨርሲቲው ይዞታ ሥር የሚገኘውን ማንኛውንም መሬት የማልማት፣ የትግበራ ዕቅድ የማዘጋጀትና ሌሎች ተያያዥ ተግባራትን አቅዶ እያከናወነ መሆኑ ተብራርቷል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲዎች እውነትንና ዕውቀትን መፈለግ ላይ እንዲያተኩሩ እና የውሳኔ አቅማቸውንና ነፃነታቸውን ከፍ ለማድረግ ብሎም የመንግሥትንና የፖለቲካ ጣልቃ ገብነትን ለማስቆም ወደ ራስ ገዝ አስተዳደር መሸጋገር ብቸኛው አማራጭ መሆኑን በማስገንዘብ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ሊያተኩሩ በሚገባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ገለጻ ሰጥተዋል፡፡ እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ማብራሪያ በ2016 ዓ/ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ወደ ራስ ገዝ አስተዳደር ከተሸጋገረ በኋላ በቀጣይ ራስ ገዝ እንዲሆኑ ባላቸው ተቋማዊ አሠራር ልምድ መሠረት ዕጩ የተደረጉ እንደ ጂማ፣ ጎንደር፣ ሐሮማያ፣ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ አርባ ምንጭ እና ሌሎችም በድምሩ 8 ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ውይይት እየተደረገ ይገኛል፡፡  

የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስትር ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ በሰጡት ማጠቃለያ የትምህርት ሚኒስቴር ዋና ዓላማው እውነትንና ዕውቀትን የሚፈልግ የኅብረተሰብ ክፍል መገንባት መሆኑን ጠቅሰው እውነትና ዕውቀት የሚገኘው ከመንግሥትና ከፖለቲካ ኃይሎች ሳይሆን በምርምር የሚፈልጓቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ከሚኖሩበት ከዩኒቨርሲቲዎች መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ከሌሎች የመንግሥት ተቋማት በተለየ ሁኔታ ያለመንግሥት ጫናና ግፊት እውነትና ዕውቀትን የመፈለግና  የማሰብ ነፃነት ያላቸው ማድረግ እንደሚገባና ይህም እንደ ማኅበረሰብና ሀገር ለመቀጠልና በዕውቀት ወደ ፊት ለመሄድ ወሳኝ መሆኑን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ገልጸዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በራስ ገዝ አስተዳደር ውጤታማ ለመሆን በተለይ ከ2014 ዓ/ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ሀገር አቀፍ  ፈተና ውጤት ትምህርት በመውሰድ ለትምህርት ጥራት ልዩ ትኩረት መስጠት፣ የፕሮግራም ኦዲት መመሪያ በማዘጋጀት ፕሮግራሞችንና ቤተ-ሙከራዎችን አክሬዲት ማስደረግ፣ ሥርዓተ ትምህርት ማሻሻል፣ ከአካባቢው ማኅበረሰብና አስተዳደር ጋር ጤናማ ግንኙነት መፍጠር፣ ውጤታማ የሆነ የመዋቅር ማሻሻያ ማድረግ ብሎም የተማሪዎች መኖሪያ፣ መማሪያና መመገቢያ እንዲሁም ማንበቢያ ቦታዎችን ምቹና ማራኪ በማድረግ ተማሪ ተመድቦ ሳይሆን መርጦ እንዲመጣ ማድረግ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት በትኩረት እንዲሠሩ ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡ ራስ ገዝነት ወይም ነፃነት ጥቅም ብቻ ሳይሆን አሁን ላይ ካለው የበለጠ ተጠያቂነትና ጉዳትም የሚኖረው በመሆኑ ከአሁኑ ጀምሮ ነፃነቱ ለሚጠይቀው ኃላፊነት በቂ ዝግጅት እስኪደረግና ዩኒቨርሲቲዎች ራሳቸውን ችለው እስከሚቆሙ ድረስ ትምህርት ሚኒስቴር በቅርበት ክትትል እያደረገ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚሰጥ ጠቁመዋል፡፡  

በውይይቱ የትምህርት ሚኒስቴርና የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችና የካውንስል አባላት ታድመዋል፡፡
 
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት