Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት የማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በኮንሶ ዞን በካራት እና ኮልሜ ክላስተር እንዲሁም በአሌ ልዩ ወረዳ በኦላንጎ በሚገኙ የነጻ ሕግ ድጋፍ መስጫ ማእከላት ላይ ግንቦት 3/2015 ዓ/ም የመስክ ምልከታ አካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በመስክ ምልከታው ላይ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ከሚሰጣቸው የማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፎች መካከል አንዱ የነጻ ሕግ ድጋፍ ሲሆን በዚህም ለኅብረተሰቡ ተደራሽ እየሆኑ ያሉ በርካታ ተግባራት እንዳሉ ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር ተክሉ አክለውም በየማእከላቱ ያሉ የዩኒቨርሲቲው የነጻ ሕግ ድጋፍ ሰጪ ባለሙያዎች ስለነጻ ሕግ ድጋፍ አገልግሎት ለኅብረተሰቡ በማሳወቅ በገንዘብ እጦት ምክንያት ፍትሕ ሳያገኙ የሚቀሩ ወገኖች ተገቢውን ፍትሕ እንዲያገኙ በማድረግ ሳይማር ያስተማራቸውን ማኅበረሰብ በትጋት ሊያገለግሉ ይገባል ብለዋል፡፡ የማኅበረሰቡን ችግር በሳይንሳዊ ጥናቶች በመፍታት ኅብረተሰቡ የተሻሉ አገልግሎቶችን እንዲያገኝ ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው በትኩራት እየሠራ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡  

የዩኒቨርሲቲው የሕግ ትምህርት ቤት ዲን መ/ር እንየው ደረሰ ምልከታው በየማእከላቱ በሕግ ት/ቤት የሚሠሩ የማኅበረሰብ አገልግሎት ተግባራት እየተከናወኑ ያሉበት ሁኔታን በመገምገም ክፍተቶችን ለመሙላትና ለመደገፍ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ መ/ር እንየው በምልከታው ወቅት በየማእከላቱ ያሉ ባለሙያዎች በንቃተ ሕግ ፈጠራ እና አቅም የሌላቸውን የማኅበረሰቡን አባላት የሕግ ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የመደገፍ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በአሌ፣ ኮንሶና ደራሼ አካባቢዎች ላይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን /UNCHR/ በ2022 የተጀመረው ድጋፍ አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን አክለዋል፡፡  

የዩኒቨርሲቲው ሕግ ትምህርት ቤት የማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ መ/ር ጌትነት ደባልቄ በበኩላቸው በነጻ የሕግ ድጋፍ መስጫ ማእከላቱ ለጠበቃ ከፍለው መከራከርና የሕግ አገልግሎትን ማግኘት ለማይችሉ አቅመ ደካሞች፣ ሴቶች፣ ሕጻናት፣ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች እንዲሁም ተፈናቃዮች በዩኒቨርሲቲው አማካኝነት ከ2004 ዓ/ም ጀምሮ ላለፉት 11 ዓመታት 12 የነጻ ሕግ ድጋፍ መስጫ ማእከላት ተከፍተው አገልግሎት እየተሰጠ እንዳለ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም ማእከላቱን በተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች በማቋቋም የማስፋፋት ሥራዎች የሚሠሩ ከመሆኑም ባሻገር እየተሰጡ ያሉ አገልግሎቶችም በኅብረተሰቡ ዘንድ ተደራሽ እንዲሆኑና ማኅበረሰቡ እያገኘ ያለውን ጠቀሜታ በመገምገም ሥራዎችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል፡፡ መ/ር ጌትነት አክለውም ከሥነ ትምህርትና ሥነ ባህርይ ሳይንስ ት/ቤት ጋር በጋራ በመቀናጀት ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ከሚሰጠው የሕግ ድጋፍ ባሻገር በተጓዳኝ የሥነ አዕምሯዊ ድጋፍ እንዲያገኙ እንደሚሠሩም መ/ር ጌትነት አመላክተዋል፡፡

በካራት ከተማና አካባቢው በርካታ ነዋሪዎች እንደመኖራቸው የነጻ ሕግ ድጋፍ ማእከል አገልግሎት ተጠቃሚዎችም ቁጥር ከፍተኛ ነው ያሉት በኮንሶ ዞን ካራት ከተማ የዩኒቨርሲቲው የነጻ ሕግ ድጋፍ መስጫ ማእከል ባለሙያ አቶ ካልጌ ለሚታ እንደተናገሩት ወደ ማእከሉ የሚመጡትን በርካታ የሕግ ጉዳዮች ወክሎ በመከራከር አብዛኞቹ መዝገቦች በሕግ ውሳኔዎችን አግኝተው ፋይሎቻቸው እንዲዘጉ ሆነዋል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ጠበቃ ገዝቶ የመከራከር አቅም ለሌላቸው የሕግ ምክር አገልግሎቶችን እና መሰል ድጋፎችን እየሰጡ መሆኑንም ባለሙያው ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይም ማእከሉ ስለሚሰጣቸው አገልግሎቶች በተለያየ መንገድ የማሳወቅ ሥራዎችን እየሠሩ እንዳሉና የነጻ ሕግ ድጋፍ ተጠቃሚ የሚሆኑ ሰዎች ከፍለው ለመከራከር አቅም የሌላቸው ስለመሆኑ ከማኅበራዊ ፍርድ ቤት የድጋፍ ደብዳቤ ይዘው ሲመጡ ከጥብቅና መቆም ጀምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ እንደሚደረግና አፈጻጸሙም ውጤታማ መሆኑን በኮንሶ ዞን በኮልሜ ክላስተር የዩኒቨርሲቲው የነጻ ሕግ ድጋፍ መስጫ ማእከል ባለሙያ አቶ ጉተማ ጉትቶ ተናግረዋል፡፡  

የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች በሰጡት አስተያየት የነጻ ሕግ ድጋፍ መስጫ ማእከላቱ በየአቅራቢያቸው መኖራቸው የተለያዩ እንግልቶችን እንደቀነሱላቸው፣ በገንዘብ ችግር አልያም በግንዛቤ እጥረት ምክንያት ፍትሕ ሳያገኙ እንዳይቀሩ የረዳቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለትራንስፖርት ምቹ ባልሆኑ ቦታዎች ጭምር ማእከላቱን በማቋቋም እየሠራ ያለው ተግባር ኅብረተሰቡን እንደጠቀመው በመግለጽ ዩኒቨርሲቲው እየሰጠ ላለው አገልግሎትም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በመስክ ምልከታውም የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፣ የሥነ ትምህርትና ሥነ ባህርይ ሳይንስ እና የሕግ ት/ቤት ዲኖች እንዲሁም የሕግ ት/ቤት የማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ ተገኝተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት