የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት የማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከጋሞ ዞን ፍትሕ መምሪያ ጋር በመተባበር በዞኑ ከሚገኙ ሦስት የከተማ አስተዳደሮችና አራት ወረዳዎች ዐቃቤያን ሕጎች፣ ወንጀል መርማሪ ፖሊሶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በወንጀል በተጠረጠሩ፣ በተያዙ እና በተከሰሱ ሰዎች መብቶች ዙሪያ ግንቦት 12/2015 ዓ/ም ውይይት አካሂዷል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የአንድ አካባቢ ኅብረተሰብ ከመልካም አስተዳደርና ከፍትሕ አኳያ እየተሻሻለ መሄድ የእድገት ምልክት መሆኑን ጠቅሰው የዩኒቨርሲቲው ሕግ ት/ቤት በሕግና ፍትሕ ዘርፍ በሚሠራቸው ዘርፈ ብዙ የማኅበረሰብ ጉድኝት ተግባራት በየዓመቱ በሀገርና በክልል ደረጃ ዕውቅናዎችን እያገኘ ነው ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ ተቋማትና የዘርፍ ኃላፊዎች ጋር ተባብሮ በመሥራት ረገድ ጠንካራ ፍላጎት ያለው በመሆኑ ትብብሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተባባሪ ፕ/ር በኃይሉ መርደኪዮስ በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲው ሕግ ት/ቤት ለዐቃቤያን ሕግና ለፖሊስ አባላት የተለያዩ የግንዛቤ ማዳበሪያ መድረኮችን በማመቻቸት ሥልጠናዎችን እየሰጠ እንደሚገኝና ከሌሎች አጋር ድርጅቶችም ጋር በመተባበር በወንጀል በተጠረጠሩና በታሰሩ ሰዎች መብት ዙሪያ በመነጋገርና ስህተቶችን በማረም የሰፈነ የፍትሕ ሥርዓት መኖሩን ለማረጋገጥ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በብዙ የዓለም ክፍሎች እስረኞች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር እያሉ የሚደርስባቸው እንግልትና ጥቃት ሰብአዊ መብታቸውን ከመጣስ ባለፈ የፍትሕ ሥርዓታችንን ታማኝነት ያጎድለዋል ያሉት ም/ፕሬዝደንቱ የታሳሪ መብት ልንገነዘበውና ልናከብረው ከሚገባን ሰብአዊ መብት አንዱና ዋነኛው በመሆኑ በጉዳዩ ላይ የሕግ ት/ቤቱና የፍትሕ አካላቱ በመወያየት፣ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት እንዲሁም አዳዲስ ሐሳቦችንና አመለካከቶችን በማምጣት ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩና የፍትሕ ሥርዓቱ ፍትሐዊ ሆኖ እንዲቀጥል በቁርጠኝነት ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡

በውይይቱ የዩኒቨርሲቲው የሕግ ትምህርት ቤት የማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ መ/ር ጌትነት ደባልቄ ስለ ነጻነትና ደኅንነት መብቶች፣ በወንጀል ተግባር ተጠርጥረው በሕግ የሚፈለጉ ተጠርጣሪዎች የሚያዙበትና የሚታሰሩበት ሕጋዊ ምክንያቶች እና ሥነ-ሥርዓታዊ አካሄዶችን ከዓለም አቀፍ ሕጎችና ልምዶች እንዲሁም ከኢትዮጵያ ሕጎች አንጻር በመቃኘት የመወያያ ሰነድ አቅርበዋል፡፡ በመወያያ ሰነዱ እንደተመለከተው በሁሉ አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መግለጫ አንቀጽ 3 ላይ እያንዳንዱ ሰው የሕይወት፣ የነጻነት እና የተሟላ የደኅንነት መብት እንዳለው ያሰፈረ ሲሆን በአንቀጽ 9 ደግሞ ማንም ሰው ያለ ሕግ አግባብ ሊያዝና ሊታሰር አይችልም፡፡ ማንኛውም  ሰው በሕግ መሠረት ሊያዝ ወይም ሊታሰር የሚችለው ሊያስይዘው ወይም ሊያስጠይቀው የሚችል የወንጀል ተግባር መፈጸሙ ሲረጋገጥ እንዲሁም የተጠረጠረበትን ወይም የተከሰሰበት የወንጀል ተግባር በሕግ መሠረት የሚያስይዘውና የሚያሳስረው መሆኑ ሲረጋገጥ ብቻ እንደሆነ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕግ እንዲሁም ሌሎች አግባብነት ያላቸው የሥነ-ሥርዓት ሕጉ ድንጋጌዎች ይዘት እንደሚያስረዱም መ/ር ጌትነት ተናግረዋል፡፡

በማስረጃና ምርመራ መርሆዎች እና እየታዩ ባሉ ክፍተቶች ላይ ሰነድ ያቀረቡት የጋሞ ዞን ፍትሕ መምሪያ ዐቃቤ ሕግ አቶ ጤናሁን ጨርቆስ የማስረጃን አስፈላጊነት ሲገልጹ ከአንድ የወንጀል ድርጊት ጋር ግንኙነት ያለው የወንጀል አድራጊውን ሁኔታ ለመለየት፣ ትክክለኛው አጥፊ ላይ ለመድረስ፣ አጥፊዎች ለፈፀሙት ሕገ ወጥ ተግባር በሕግ  እንዲጠየቁ  ለማድረግ፣ በፍትሕ ሥርዓት አሠራር ውስጥ ጊዜንና ገንዘብን ለመቆጠብ እና የሐሰት ክስንና ምስክርነትን ለመቆጣጠር እንዲሁም የተሳሳተ ውሳኔ እንዳይወሰን ያግዛል ብለዋል፡፡

አቶ ጤናሁን አክለውም መዛግብት ላይ ከሚታዩ ክፍተቶች በቃለ መጠይቅ ደረጃ የተሰበሰበ መረጃን የማደራጀት ክፍተት፣ ቃለ መጠየቅ ላይ ሊነሱና ሊያልቁ የሚገቡ ጉዳዮች የምርመራው አካል ሆነው መቅረባቸው፣ ምስክሩ  እንዳልመሰከረ እየታወቀ ቃሉ የምርመራው አካል ተደርጎ የሚላኩ መዝገቦች መብዛታቸው፣ ምስክሮች በአንድ ጉዳይ ስለተለያየ ፍሬ ነገር እያስረዱ  በትክክል ሳይጠራ መዝገቡ ለዐቃቤ ሕግ የሚላክ መሆኑ፣ ተበዳይ ወገን ለምስክርነት የላከውን በሙሉ ቃል መቀበል፣ ዐቃቤ ሕግ ይለየው በማለት እንዳልተመሰከረበት እየታወቀ መዝገብ ውስጥ አካቶ መላክና ግለሰቡን አስሮ ማቆየት ተጠቃሾች ናቸው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም አለአግባብ ስለሚዘጉ መዛግብት እና የይጣራልን አቤቱታዎች በስፋት ገልጸዋል፡፡

የውይይት መድረኩ የሕግ ማስከበር ሥራዎች እንዴት እየተሠሩ እንደነበርና በቀጣይ እንዴት መሠራት እንዳለባቸው በማሰብ ክፍተቶችን ለይቶ የእርምት እርምጃ ለመውሰድ የሚያነቃቃ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው የሕግ ትምህርት ቤት ዲን መ/ር እንየው ደረሰ ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ ከዞኑ ፍትሕ መምሪያ ጋር በመቀናጀት ከተለያዩ በጀት ካላቸው ተቋማት ጋር በመነጋገር እንደ ዞን ክፍተቶችን በመለየትና የተሻሉ አሠራሮችን በማምጣት የዜጎች መብትና ፍትሕ እንዲከበር በተቀናጀ መንገድ ሥራዎች እንደሚሠሩና የተለያዩ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎችና የውይይት መድረኮችን እንደሚያዘጋጁ መ/ር እንየው ጠቁመዋል፡፡

‹‹መነሻችን ምርመራ መድረሻችን ደግሞ አርሞ ማነጽ ነው›› ያሉት የጋሞ ዞን ፍትሕ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሽመልስ ጮራ ከውይይቱ በኋላ የተሠሩ ሥራዎችን ወደ ኋላ ተመልሶ በማየት ክፍተቶቻችንን በመለየትና ትክክለኛ ምርመራዎችን በማካሄድ አላስፈላጊ ውሳኔዎችን ላለመወሰን አቋም ልንይዝ ይገባል ብለዋል፡፡ በቀጣይም እንደ ዐቃቤ ሕግ፣ ፖሊስ መዋቅርና እንደ ፍርድ ቤት መውሰድ ያለብንን ኃላፊነት ከፋፍለን ለመሄድ በጸጥታ መዋቅሩ ላይ የመወያያ መድረኮችን በማዘጋጀት ስህተቶችን በመነጋገርና በማረም ዞኑን የሚመጥን የፍትሕ ተቋም ለመገንባትና አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት መሥራት  እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ ከምርመራ ሥርዓቶች ጋር ያሉ ክፍተቶችን ለመቅረፍ ያስችል ዘንድ በዩኒቨርሲቲው ያለውን የፎረንሲክ ኬሚስትሪ ማሽን በመጠቀም የሚሠራበት መንገድ ቢመቻች መልካም ነው ያሉት አቶ ሽመልስ ዩኒቨርሲቲውም የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

በመጨረሻም በተነሱ ርእሰ ጉዳዮች ላይ በፍትሕ አካላቱ ዘንድ ያሉ ክፍተቶችና ሊሻሻሉ የሚገቡ ጉዳዮች ተነስተው ሰፊ ውይይትና ምክክር ተካሂዶባቸዋል፡፡ በውይይት መድረኩ የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት፣ የአርባ ምንጭ ከተማና ዙሪያ ወረዳ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንቶች፣ በዞኑ ከሚገኙ ሦስት የከተማ አስተዳደሮችና አራት ወረዳዎች ዐቃቤያን ሕጎች፣ ወንጀል መርማሪ ፖሊሶች፣ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት፣ ም/ፕሬዝደንት እና የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እንዲሁም የሕግ ት/ቤት ዲንና መምህራን ተገኝተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት