የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ማኅበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከራእይ ፕሮጀክት እና ከአርባ ምንጭ ከተማ ሴቶችና ሕፃናት ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ከውሃ ምንጭ ቀበሌ ሃይላንድ መንደር ለተወጣጡ በእንጨት ለቀማ ለሚተዳደሩና በፕሮጀክቱ ለታቀፉ 91 ሴቶች ሐምሌ 7/2015 ዓ/ም የሕይወት ክሂሎትና ሥራ ፈጠራ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ዩኒቨርሲቲው አጋር ድርጅቶችን በማሳተፍ ለማኅበሩ የሼድ ድጋፍ በማድረግ የመሥሪያ ቦታ ግንባታ መጀመሩን ጠቁመው ሠልጣኞቹ በሦስት ማኅበራት ተደራጅተው ወደ ሥራ እንደሚሰማሩ ተናግረዋል፡፡ ሴቶችን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ከደን እንጨት ከመልቀም ሕይወት መታደግ ብሎም በፓርኩ ላይ የሚደርሰውን ተጽእኖ መቀነስ ከፕሮጀክቱ ዓላማዎች የሚጠቀሱ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ማኅበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊና የፕሮጀክቱ አባል ወ/ሮ አስቴር ሰይፉ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ በእንጨት ለቀማ የሚተዳደሩ ሴቶችን ወደ ዕደ ጥበብ እና ሌሎች የሥራ ዘርፎች በማሰማራት አኗኗራቸውን ማሻሻል ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡ በሥራቸው ውጤት ማምጣት እንዲችሉ ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት የዕውቀት ክፍተታቸውን ለመሙላት ሥልጠናው የተሰጠ ሲሆን በቀጣይም የማሽኖች ግዥ ሲፈጸም ቴክኒካል የሆኑ ሥልጠናዎችን እንደሚወስዱ አመላክተዋል፡፡ የወርክሾፕ ግንባታዎችን በማጠናቀቅና አስፈላጊ ግብአቶችን በማሟላት በሕይወታቸው ላይ ዘላቂ ለውጥ እስኪመጣ ክትትልና ድጋፎች እንደሚቀጥሉ እና ፕሮጀክቱ ዘላቂነት ኖሮት ሌሎች መሰል የአካባቢውን ማኅበረሰብ ለማገዝ ድጋፉ እንደሚቀጥል ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ከተማ ሴቶችና ሕፃናት ጉ/ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ማሕሌት ደፈርሻ በከተማው በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሴቶች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ኢኮኖሚያቸውን ለማበልጸግና አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ በጋራ እየሠራን ነው ብለዋል፡፡

የፕሮጀክቱ አባልና አሠልጣኝ መምህርት ዐይናለም ሞገስ በሥልጠናው ዕለት ከዕለት የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች እንዴት መፍታት እንዳለባቸው፣ የግጭት አፈታት፣ የጋራ ዓላማን ለማሳካት እንዴት መሥራት እንደሚገባ እና የቢዝነስ ክሂሎት ርእሰ ጉዳዮችን መዳሰሳቸውን ገልጸው ከሠልጣኞችም በርካታ ከተማዋን የሚጠቅሙ የቢዝነስ ሃሳቦች መነሳታቸውን ተናግረዋል፡፡

የራእይ ፕሮጀክት የወጣቶች ሥራ ፈጠራ አማካሪ አቶ አብነት ጴጥሮስ እንደገለጹት በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ወጣቶችና በእንጨት ለቀማ የሚተዳደሩ ወገኖችን ያለባቸውን የኢኮኖሚ ችግር ታሳቢ በማድረግ በጋራ አደራጅቶ በማሠልጠን ወደ ዕደ ጥበብ ሥራ እንዲሰማሩ ለማድረግ ሥልጠናው ተዘጋጅቷል፡፡

አቶ አብነት ሥልጠናው የሕይወት፣ የንግድና የፋይናንስ ክሂሎት ላይ ትኩረት ያደረገና ወጪው ሙሉ በሙሉ በፕሮጀክቱ የሚሸፈን መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው እና በከተማ አስተዳደሩ በኩል የሼድ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው የጠቀሱት አቶ አብነት የመሥሪያ ቦታ ግንባታ እየተካሄደ መሆኑንና አስፈላጊ ግብአቶችን ለማሟላት ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛልም ብለዋል፡፡

የፕሮጀክቱ አባልና ሠልጣኝ የሆኑት ወ/ሮ ሙሉነሽ ሙሽሬ በእንጨት ለቀማ ሥራ ልጆቻቸውን እንደሚያስተዳድሩ ገልጸው በፕሮጀክቱ በመታቀፋቸውና ሥልጠናውን በመሳተፋቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡ የሥራ ተነሳሽነትን የሚጨምሩና ራስን ለመለወጥ የሚረዱ ሃሳቦችን ከሥልጠናው ማግኘታቸውንም ገልጸዋል፡፡

ለበርካታ ዓመታት በእንጨት ለቀማና ሽያጭ ላይ እንደቆዩ የተናገሩት ሌላኛዋ ሠልጣኝ ወ/ሮ ጌጤነሽ ኬቦ ሥራው ጾታዊ ጥቃቶች፣ በሕግ አካላት የሚወሰዱ እርምጃዎች፣ የመሸጫ ቦታ ርቀት እና መሰል ችግሮች ያሉበት በመሆኑ ከዚያ ሕይወት እንድንወጣ የተጀመረው ሥራ አስደሳችና የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡ ከሥልጠናው ያገኙትን ጠቃሚ ሃሳብ ወደ ተግባር መቀየር እንደሚጠበቅባቸውም አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት