አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የዩኒቨርሲቲው ምሩቃን በሀገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ተቋማት በሚቀጠሩበት ወይም ተቀጥረው እየሠሩ ባሉበት ጊዜ የሚቀርቡ የትምህርት ማስረጃ ትክክለኛነት ይጣራልን ጥያቄዎችን እየተቀበለ የትምህርት ማስረጃ አጣርቶ በማረጋገጥ በተከታታይ ምላሽ በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

በዚህም መሠረት በ2015 ዓ/ም የቀረቡ የትምህርት ማስረጃ ማጣራት ጥያቄዎችን ተከትሎ በተደረገ የማጣራት ሂደት ከአንዳንድ ተቋማት የቀረቡ የዩኒቨርሲቲው ምሩቃን የትምህርት ማስረጃዎች በዩኒቨርሲቲው በተሰጣቸው የተማሪ ውጤት ኮፒ ላይ የአጠቃላይ ነጥብ ለውጥ የተደረገባቸው እንዲሁም ፈጽሞ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ያልተማሩባቸው ሐሰተኛ ዲግሪ ማስረጃዎች ሆነው የተገኙ መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡

በመሆኑም መሰል ኃላፊነት የጎደላቸው ተግባራት እንዳይበረታቱ ብሎም ሕዝብና መንግሥት ሙያዊ ብቃት በሌላቸውና ኃላፊነት በጎደላቸው ዜጎች ለጉዳት እንዳይጋለጥ በማሰብ በዩኒቨርሲቲው የትምህርት ማስረጃ ላይ የዘመኑን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ በማስመሰልና በመቀየር እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው ስምና ሎጎ ያልተማሩበትን ዲግሪ ይዘው የማጭበርበር ተግባር ላይ የተሠማሩና ወደ ፊትም የሚሠማሩ ቢኖሩ ለሕዝብ የማጋለጥ ሥራ በተከታታይነት እንዲሠራ ዩኒቨርሲቲው ወስኗል፡፡ ስለሆነም ከዚህ መግለጫ ጋር በፎቶ በተያያዘው የሐሰተኛ ማስረጃ ማጣራት ሪፖርት ላይ ስማቸው የተጠቀሱ ግለሰቦች በእነዚህ የትምህርት ማስረጃዎች በየትኛውም ተቋም ቢቀጠሩ ማስረጃዎቻቸው ሕጋዊነት የሌላቸው መሆኑን ማረጋገጣችንን እናሳውቃለን፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት