አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ2016 በጀት ዓመት ዓመታዊ ዕቅዱን በዩኒቨርሲቲው ካውንስል ነሐሴ 5/2015 ዓ/ም አስገምግሟል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የበጀት ዓመቱ ዕቅድ በስትራቴጂክ ዕቅዱ መካከለኛ ጊዜ (2016-2018) ያለውን የትምህርት ልማት ዕቅድን መሠረት አድርጎ የተዘጋጀ ሲሆን የትምህርት ጥራት፣ አግባብነት፣ ተደራሽነትንና ፍትሐዊነትን ማረጋገጥ፣ የምርምርና ፈጠራ ሥራዎች ተደራሽነትና ፍትሐዊነት እንዲሁም የሀገር በቀል ዕውቀትን ማጣጣምና ማሳደግ፣  የማኅበረሰብ ጉድኝትና የሳይንስ ባህል ግንባታ ተደራሽነትና ፍትሐዊነትን ማሳደግ፣ የተቋማት ትስስርና ተሳትፎ፣ ሥራ ፈጠራ፣ ቴክኖሎጂ ሽግግርን እና ዓለም አቀፍ አጋርነትን ማሳደግ፣ የትምህርት አመራርና አስተዳደርን ማጠናከር፣ የትምህርት ተቋማዊ አቅምና ብቃት ማጎልበት፣ የትምህርት መሠረተ ልማትና ፋሲሊቲ ማሳደግ እንዲሁም የሀብት ምንጭና አጠቃቀም ውጤታማነትን ማሳደግ የበጀት ዓመቱ ዕቅድ የተጠቃለሉ ስትራቴጂያዊ ግቦች ናቸው፡፡

የስትራቴጂክ ዕቅድ ዝግጅት፣ ትግበራና ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ሰለሞን ይፍሩ ባቀረቡት የበጀት ዓመቱ የዕቅድ ሰነድ ላይ እንደተመላከተው በመደበኛ ትምህርት መርሃ ግብር የሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራሞችን ቁጥር ከ140 ወደ 150 ማሳደግ፣ የሦስተኛ ዲግሪ ፕሮግራሞችን ቁጥር ከ34 ወደ 39 ማሳደግ፣ በትምህርት ሚኒስቴር የሚሰጠዉን የመውጫ ፈተና ተግባራዊ ማድረግ፣ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ተሳትፎን ከ273 ወደ 445 ማድረስ፣ የተማሪዎች ማጠናቀቅ ምጣኔ በመጀመሪያ ዲግሪ ከ76.04 በመቶ ወደ 80 በመቶ፣ በሁለተኛ ዲግሪ ከ 60 በመቶ ወደ 95 በመቶ እና በሦስተኛ ዲግሪ ከሰባት በመቶ ወደ 55 በመቶ ማድረስ፣ በሀገር ውስጥ የሦስተኛ ዲግሪ ትምህርት ዕድል ለ40 መምህራንና በውጭ ሀገር ለ20 መምህራን መስጠት የሚሉት በመማር ማስተማሩ መስክ በበጀት ዓመቱ ለመፈጸም ከተያዙ ዐበይት ተግባራት መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

የምርምር ልኅቀት ማዕከላትን ከስምንት ወደ ዘጠኝ ማሳደግ እንዲሁም የመስክ ምርምር ሠርቶ ማሳያ ማዕከላትን ብዛት አምስት ማድረስ፣ ስድስት የምርምር ሲምፖዚየሞችን ማዘጋጀት፣ ዕውቅና (Accreditation) ያገኙ የዩኒቨርሲቲዉ ጆርናል ብዛትን ከአንድ ወደ ሁለት ማሳደግ፣ 754 የምርምር ውጤቶችን በማሳተም ለተጠቃሚዎች ማድረስ፣ ለምርምር የሚውል ገንዘብ ለማመንጨት የተቀረጹ ፕሮጀክቶችን ቁጥር ከ30 ወደ 40 ማሳደግ፣ አራት የተላመዱና ችግር ፈቺ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ለማኅበረሰቡ ማሸጋገር፣ አራት ቴክኖሎጂዎችን በመለየት ፕሮቶታይፓቸው እንዲሠራ ዝግጁ ማድረግ፣ የሀገር በቀል ዕውቀቶች ላይ ትኩረት አድርገው የሚሠሩ ምርምሮችን ብዛት ከ17 ወደ 25 ማሳደግን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ተግባራት በምርምር፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና ማኅ/ጉድኝት መስክ ለመፈጸም በዕቅድ የተያዙ ናቸው፡፡

በተጨማሪም ለ6,950 የማኅበረሰብ ክፍሎች ነፃ የሕግ ጥብቅና፣ ምክር አገልግሎትና ሠነድ ዝግጅት አገልግሎቶችን መስጠት፣  11 ችግር ፈቺ የሆኑ የማኅበረሰብ ልማት ፕሮጀክቶችን በመተግበር ስምንቱን ፕሮጀክቶች በማጠናቀቅ ማኅበረሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ፣ 26,000 ችግኞችን በስድስተኛው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር መትከልና 1.71 ሚሊየን ለተከላ የደረሱ ችግኞችን ማሰራጨት በምርምር. ቴክኖሎጂ ሽግግርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፍ በበጀት ዓመቱ እንዲፈጸሙ ከታያዙ ተግባራት መካከል መሆናቸው በተዘጋጀው ዓመታዊ ዕቅድ ተመላክቷል፡፡

በከፍተኛ ተቋማት የመረጃ ሥርዓት (HIMS) ላይ የዩኒቨርሲቲውን መረጃዎች ሙሉ በሙሉ ማስገባት እንዲሁም በየጊዜዉ መከለስ፣ የሦስት ሕንጻዎች መልሶ ግንባታና ሦስት ሕንጻዎች ዕድሳት ማካሄድ፣ የዩኒቨርሲቲዉ የከፍተኛ ፍጥነትና ተመጣጣኝ የብሮድባንድ ኢንተርኔት ተጠቃሚነትን ከ 2.8 ጊባ(GB) ወደ አራት ጊባ(GB)  ማሳደግ፣ ሁሉም ካምፓሶች የተሟላ፣ ውብና ማራኪ መልክዓ ምድር (Landscape) እንዲኖራቸዉ 10,000 ካሬ ላንድስኬፕ ሥራ መሥራት፤ የማኅበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ ግንባታን በማጠናቀቅ ጣቢያውን ማቋቋምና ሥራ ማስጀመር፣ ያደገ ተቋማዊ ገቢን ከ75 ሚሊየን ወደ 100 ሚሊየን ማሳደግና  ከዓመታዊ መደበኛ በጀት የውስጥ ገቢ ድርሻን ወደ 8.3 በመቶ ማድረስ፣ በበጀት ዓመቱ የሚጠናቀቁ በሂደት ላይ ካሉ 20 ነባር የግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል ሦስት ጊዜያዊና አምስት አጠቃላይ ርክክብ በማድረግ ግንባታዎችን ወደ ሥራ ማስገባት፣ የ860 ካሬ የጌጠኛ ኮብል ድንጋይ ንጣፍ አስፈላጊ በሆኑ መንገዶች ላይ ማሠራት የሚሉት ተግባራት በአስተዳደርና ልማት ዘርፍ እንዲፈጸሙ ከተወጠኑ ዋና ዋና ሥራዎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ለ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ ማስፈጸሚያ ለዩኒቨርሲቲው መደበኛ በጀት ብር 1,210,714,400 እና ካፒታል በጀት ብር 200,000,000 በድምሩ ብር 1,410,714,400 መመደቡ በዕለቱ የተገለጸ ሲሆን ሁሉም የሥራ ኃላፊዎች የበጀት ዓመቱን ዕቅድ እስከ ግለሰብ ባለሙያ ድረስ ወርዶ እንዲታቀድ በማድረግ ለዕቅዱ ተግባራዊነት በትጋት እንዲሠሩ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በሰጡት የማጠቃለያ ሃሳብ በአጽንኦት አሳስበዋል፡፡

 አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

 

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት