የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት የማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን/UNHCR/ ጋር በመተባበር በአሌ ልዩ ወረዳ ከሚገኙ 17 ቀበሌያት ለተወጣጡ 34 የማኅበራዊ ፍርድ ቤት ዳኞች በሰብዓዊ መብቶች እና ፆታን መሠረት ባደረጉ ጥቃቶች ላይ ነሐሴ 11/2015 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡  ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የሕግ ትምህርት ቤት ዲን መምህር እንየው ደረሰ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ባሻገር በምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፎች በሚደርስባቸው አካባቢዎች የኅብረተሰቡን ችግር ምርምርን መሠረት ባደረገ ሁኔታ በመፍታትና አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመው ት/ቤቱ ባሉት የነጻ ሕግ ድጋፍ መስጫ ማዕከላትም አቅም ለሌላቸው ሴቶች፣ ሕጻናት፣ አረጋውያንና ተፈናቃይ ወገኖች የነጻ ሕግ ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የማኅበራዊ ፍርድ ቤት ዳኞችን አቅም በማጎልበት የሕዝቡ ሰብዓዊ መብት እንዳይጣስና የሚጥሰውም አካል ተገቢውን ቅጣት እንዲሁም ተጎጂውም ፍትሕ እንዲያገኙ ለማስቻል እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በመደጋገፍ ልንሠራ ይገባል ብለዋል፡፡ አክለውም በማኅበራዊ ፍርድ ቤቶች ላይም ሆነ በሌሎች የሥራ መስኮች ላይ ሴቶችን ማሳተፍ እንደሚገባ መ/ር እንየው ተናግረዋል፡፡  

በሰብዓዊ መብቶች ላይ ሥልጠና የሰጡት የዩኒቨርሲቲው ሕግ ትምህርት ቤት የማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ መ/ር ጌትነት ደባልቄ እንደገለጹት የሰብዓዊ መብቶች የዘር፣ የሐይማኖት፣ የቀለምና የጾታ ልዩነት ሳይኖር የሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ብቻ በተፈጥሮ ያገኛቸው መብቶች ሲሆኑ እነዚህም መብቶች የማይገፈፉ፣ የማይገረሰሱ፣ ዓለማቀፋዊና የማይነጣጠሉ ናቸው፡፡  ከዚህም ባሻገር የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የሕግ መግለጫ ሁሉ ዓቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ ሲሆን በዚህም ድንጋጌ ውስጥ ማንኛውም ሰው የሕይወት፣ የነጻነት፣ የደኅንነት፣ ከባርነትና ከግዴታ አገልጋይነት፣ ከጭካኔና ከኢ-ሰብዓዊ አያያዝ የመጠበቅና በሕግ ፊት እኩል የመታየት መብት ያለው መሆኑን አሠልጣኙ ጠቅሰዋል፡፡

በሌላ በኩል የሕጻናት መብቶችን አስመልክተው ሕጻናት የአስገድዶ መደፈር ጥቃትና የሌሎች ሰብዓዊ መብቶቻቸው ጥሰት ይደርሱባቸዋል ያሉት መ/ር ጌትነት ሕጻናት እንደማንኛውም ሰው የመውረስ መብት ያላቸው በመሆኑ መብቶቻቸው ሲጣሱ ልናስከብርላቸውና ጥብቅና ልንቆምላቸው እንደሚገባ ገልጸው የነጻ የሕግ ድጋፍ መስጫ ማዕከላቱም ሚና መሰል ተግባራትን መደገፍ መሆኑን አክለው ተናግረዋል፡፡

ፆታና ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች በሚል ርዕስ ሥልጠና የሰጡት ሌላኛዋ አሠልጣኝ የዩኒቨርሲቲው ሕግ ትምህርት ቤት መ/ርት ማህሌት ደመቀ ፆታን መሠረት በማድረግ በሴቶች ላይ የሚደርሰውና የደረሰው ተጨማሪ በደል ዕውቅና አግኝቶ ማስተካከያ መንገድ ካልተበጀለት ሴቶች ለዜጎች በተደነገጉት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ብቻ ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደማይችሉና ለሴት ልጆች የሚሰጡ ቦታዎችና ትኩረቶች አናሳ ናቸው ብለዋል፡፡ ምንም እንኳን ሴቶች እንደዜጋ መብት የተሰጣቸው ቢሆንም እንደሌላው የማኅበረሰብ ክፍል የተሰጣቸውን መብት በእኩል የመጠቀም ደረጃ ላይ ለመድረስ ከሌላው ማኅበረሰብ በተለየ ከለላና ጥበቃ እንደሚያስፈልጋቸው የኢትዮዮጵያ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 35(1) ላይ የሚያረጋገግጥ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በመሆኑም ለሴት እህቶቻችን መብት ከመስጠትና ልዩ ጥበቃ ከማድረግ ባለፈ ከሌላው ማኅበረሰብ ጋር እኩል እንዲራመዱ፣ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማበረታታት፣ ማስተማር እንደሚያስፈልግና የሚደርሱባቸውን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነ - ልቦናዊ ጥቃቶችን ለመከላከልና ለማስቀረት ከወረዳ ጀምሮ እስከ ቀበሌያት ድረስ ወርዶ ማኅበረሰቡን በማስተማር ያለውን የአመለካከት ክፍተት ለመቅረፍ ተባብረን ልንሠራ ይገባል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የሕጻናት መብት ኮንቬንሽን አጠቃላይ መርህ፣ የወንጀል ሕግ፣ የአካል ጉዳተኞች መብት፣  በዓለም አቀፍና በአህጉር አቀፍ የወጡ የሕግ ማዕቀፎች እና ድንጋጌዎች እንዲሁም በሀገራችን ያሉ የሕግ ማዕቀፎች፣ የሴቶች መብት በዓለም አቀፍ ስምምነት በሥልጠናው ትኩረት የተሰጠባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡

የአሌ ልዩ ወረዳ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት አቶ ሽመልስ አወቀ ዩኒቨርሲቲው በተለያየ ጊዜ ሥልጠናዎችን በመስጠት በየማዕከላቱ የሕግ ባለሙያዎችን በመቅጠር፣ የሕዝቡን ችግር በመጋራትና መፍትሄዎችን በመስጠት እያደረገ ላለው መልካም ተግባር አመስግነዋል፡፡ ፕሬዝደንቱ አክለውም ሠልጣኞች የተፈናቃዮችን፣ የሕጻናትን፣ የሴቶችንና የአረጋውያንን መብት ለማስጠበቅና ለመርዳት በሚደረገው ጥረት ከቀድሞው በተሻለ ሁኔታ ከማዕከሉ የሕግ ባለሙያ ጎን በመሆን በሕጉ መሠረት ተገቢውን ድጋፍና ትብብር እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡  

ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት በቀጣይ ሴት ልጆች ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱና እንዲማሩ፣ ያለዕድሜያቸው ትዳር እንዳይፈጽሙና መብቶቻቸው እንዲከበሩ ሌሎችንም በማስተማር በኅብረተሰቡ ዘንድ በሂደት ለውጥ ለማምጣት እንሠራለን ብለዋል፡፡  

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት