የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ትምህርትና ሥነ ባሕርይ ት/ቤት ከጫሞ ካምፓስ የፀረ-ኤች አይ ቪ/ኤድስና ሥነ ተዋልዶ ጤና ማስተባበሪያ ጋር በመተባበር ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን አስመልክቶ የልባም ሴት የስኬት ምሥጢር፣ የጾታዊ ጥቃት ምንነት እና ተያያዥ ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ መጋቢት 07/2016 ዓ/ም የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

በዩኒቨርሲቲው ሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት የጫሞ ካምፓስ የፀረ-ኤች አይ ቪ/ኤድስና ሥነ ተዋልዶ ጤና አስተባባሪ አቶ ተራመድ ታደሰ እንደገለጹት ሥልጠናው ሴት ተማሪዎች በት/ቤትና ከት/ቤት ውጭ የሚገጥሟቸውን ሁለንተናዊ ተግዳሮቶች በማሸነፍ ዓላማቸውን እንዲያሳኩ፣ በራስ መተማመናቸው እንዲጎለብት፣ ጤናማ ዜጋ እንዲሆኑ እንዲሁም ለቀጣዩ የትምህርት ደረጃ በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ ያለመ ነው፡፡

ለሥነ ተዋልዶ ጤናና ተያያዥ የጤና ችግሮች የሚዳርጉ የአቻ ግፊት፣ ቅጥ ያጣ የነጻነት ስሜት እንዲሁም ራስን ለአጋላጭ ድርጊቶች አሳልፎ መስጠት መዘዙ የከፋ በመሆኑ ሴት ተማሪዎች ከአላስፈላጊ ድርጊቶች ባህሪያት በመቆጠብ ሁል ጊዜ ልባም ሴት የመሆን ፍላጎት ላይ ትኩረት ሊያደርጉ እንደሚገባ አስተባባሪው አሳስበዋል፡፡

የሥነ ባሕርይ ት/ክፍል መምህርት ኑኃሚን የኔሰው ልባም ሴት እውነተኛ ሕልም ያላትና ቆራጥ ሴት ስትሆን ዓላማዋን ከግብ ለማድረስ በሌሎች ጥገኛ የማትሆንና በጥረት የምታምን መሆኗን ተናግረዋል፡፡ እንደ መ/ርት ኑኃሚን ሴትነት የድክመት ሳይሆን የጥንካሬ መገለጫ ሲሆን ለዚህም በጥረታቸው ከወንዶች በተሻለ የስኬት ሕይወት የሚገኙትን ምሳሌ መውሰድ አስፈላጊ ነው፡፡

የስኬታማ ሴት ምሥጢር ዓላማን ትኩረት አድርጎ በተነሳሽነት መሥራትና ግብን ወደ ተግባር መቀየር እንደሆነ የገለጹት መ/ርት ኑኃሚን ሴት ተማሪዎች አልችልም ባይነትን በማስወገድ፣ ለራሳቸው ክብር በመስጠት፣ ከውድቀት በመማር እንዲሁም ለስኬታማ ጉዞ የሚያስፈልጉ ጉዳዮችን በመምረጥ ለዓላማቸው እውን መሆን መዘጋጀት እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡

የጫሞ 2 ደረጃ ት/ቤት ም/ር/መ/ር አቶ የአቦወርቅ ግርማ በበኩላቸው ሥልጠናው የሴት ተማሪዎችን የመማር ፍላጎትና ተነሳሽነት በመጨመር ውጤታቸው እንዲሻሻል ከማገዙም ባሻገር የተወዳዳሪነት መንፈሳቸው እንዲጎለብት ያግዛል ብለዋል፡፡

ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው ከድክመት ይልቅ ብርታትን፣ ከውድቀት መነሳትን እንዲሁም ልባም ሴት ለመሆን ከስኬታማ ሴቶች መማር እንደሚቻል የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሥልጠናው መዝጊያ የኢትዮጵያ ስኬታማ ሴቶችን የሚዘክር የጥያቄና መልስ ውድድር የተካሄደ ሲሆን በት/ቤቱ የትምህርት ተሳትፎ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ከ9-11 ክፍል ሴት ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት