Print

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ሀገር በቀል ዕውቀት ለሥራ ፈጠራ፣ ለቁጠባና ለዘላቂ ሰላም በሚል ርእስ ሀገር አቀፍ የምርምር ዐውደ ጥናት ሚያዝያ 19/2016 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንትና የፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ ባስተላለፉት የእንኳን ደኅና መጣችሁ መልእክት ሀገራችን በርካታ ሀገር በቀል ዕውቀቶች ያሏት ቢሆንም ያለንን ከማዳበር ይልቅ ከውጪ የመጣን የማድነቅና የራስን ኋላ ቀር አድርጎ የማየት አባዜ ተጠናውቶናል ብለዋል፡፡ በሀገራችን ከሥራ ፈጠራና ቁጠባ አንጻር ምሳሌ የሚሆኑ የተለያዩ ሀገር በቀል ዕውቀቶች መኖራቸውን የጠቀሱት ዶ/ር ዓለማየሁ በርካታ ነጋዴዎች ሥራዎቻቸውን ለማስፋፋት፣ አዳዲስ የሥራ ዘርፍ ለመጀመርና ለሌሎችም ዓላማዎች የሚጠቀሙበትን እቁብ ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ በሀገር በቀል ዕውቀት ዘላቂ ሰላምን ከማስጠበቅ አኳያ የጋሞ ዱቡሻ፣ የኦሮሞ ገዳ እንዲሁም በአማራና በሌሎች አካባቢዎች ሽምግልና የሚባሉ የግጭት መፍቻ፣ ሰላም ማውረጃ፣ የተበደለ መካሻ እና  የአመራር ሥርዓቶች መኖራቸውን ም/ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ወርቅነሽ ብሩ ሀገሪቷ ያሏት ባህላዊ ሀብቶችና ዕውቀቶች ተጠብቀውና ለምተው ለተተኪው ትውልድ እንዲተላለፉ ማስቻል እንዲሁም ዜጎች ከሀብቶቹ ጥቅም የሚያገኙበትን ሁኔታ ከፍ ማድረግ ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከተሰጡ ኃላፊነቶች መካከል መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት መንግሥት ሀገር በቀል ዕውቀቶችን በመጠቀም በሀገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች የሚስተዋሉ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝም ሚኒስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል፡፡ መሰል መድረኮች ሀገር በቀል ዕውቀቶችን በመሰነድ፣ በማጥናትና በማልማት ለሀገራዊ ብልጽግና ቁልፍ የልማት መሣሪያ ለማድረግ አቅጣጫ የሚያመላክቱ ሃሳቦች በማፍለቅ ረገድ ጉልህ ሚና ይጫወታሉም ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የባህልና ቋንቋ ምርምር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶ/ር ሰኢድ አሕመድ እንደተናገሩት 7ኛው ሀገር አቀፍ የሀገር በቀል ዕውቆቶች ለዘላቂ ሰላም ሲምፖዚየም የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ባህልና ቋንቋ ምርምር ኢንስቲትዩት እና ከዩኒቨርሲቲው የሥራ ፈጠራ ልማት ማበልጸጊያ ማዕከል ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን ዓላማውም ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ለሥራ ፈጠራ፣ ለቁጠባ ባህል መዳበርና ለዘላቂ ሀገራዊ ሰላም ከመጠቀም አኳያ ያላቸውን ፋይዳ ማስገንዘብ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ጉባዔው ታዋቂ ምሁራን ሙያዊ አስተያየቶችን የሰጡበትና የምርምር ውጤቶችን ያቀረቡበት መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ሰኢድ ወጣቱን ሀገር በቀል ዕውቀቶችን በመጠቀም ሥራ ፈጣሪና ቆጣቢ እንዲሆን ማስቻል ሌላኛው የዓውደ ጥናቱ ትኩረት እንደነበር አውስተዋል፡፡

ከዕለቱ ቁልፍ መልእክት አቅራቢዎች መካከል የቀድሞ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር አሰፋ ባልቻ በሀገራችን እምብዛም ጥቅም ላይ ያልዋሉ ከመድኃኒትና ሕክምና፣ ከተፈጥሮ ሀብት አያያዝ፣ ከቤተሰብ ምጣኔ፣ ከሥነ ምግብ ቴክኖሎጂ፣ ከተባይ ቁጥጥር፣ ከዕደ ጥበብና ከሌሎች ዘርፎች ጋር የተገናኙ በርካታ ሀገር በቀል ዕውቀቶች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ እነዚህን ሀገር በቀል ዕውቀቶች በአግባቡ መጠቀም መቻል ከሥራ ዕድል ፈጠራ ባሻገር ሁለንተናዊ ሀገራዊ እድገትና ልማት ለማስመዝገብ በእጅጉ የሚጠቅም መሆኑን ዶ/ር አሰፋ ተናግረዋል፡፡ እየጠፉ የሚገኙ ሀገር በቀል ዕውቀቶች በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ  አለመዋላቸውና መፍትሔዎችን ሁሉ ከምዕራቡ ዓለም መጠበቃችን ችግር ውስጥ ከትቶናል ያሉት ዶ/ር አሰፋ የራሳችንን ችግሮች መፍታት የሚያስችሉ ቁልፎች በእጃችን ያሉ በመሆኑ ወደ ራሳችን እንመልከት በማለት ንግግራቸውን ቋጭተዋል፡፡

እንግሊዝ ሀገር በሚገኘው ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት ሌላኛው ቁልፍ መልእክት አቅራቢ ዶ/ር ታደሰ ወልዴ በበኩላቸው በሀገራችን እንደ ዱቡሻ ያሉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለቸው ሀገር በቀል ዕውቀቶችና የአስተዳደር ሥርዓቶች መኖራቸውን ጠቁመው ዱቡሻ በውስጡ የተለያዩ ክፍሎች ያሉት ትልቅ ሥርዓት ያለው በመሆኑ የሥርዓቱን ሙሉ ክፍል ለመመለስ ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡ የዱቡሻዎች መኖር ብቻ በቂ አለመሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ታደሰ እየተቀዛቀዘ የመጣውን ይህንን ሥርዓት በአግባቡ የሚጠቀሙ ሰዎችን ዳግም መፍጠር ይገባልም ብለዋል፡፡ መጥፋት የሌለባቸው ብዙ ነገሮች እየጠፉ መሆናቸውን በቁልፍ ንግግራቸው የጠቆሙት ዶ/ር ታደሰ መሰል ሀገር በቀል ዕውቀቶችና ቦታዎችን በአግባቡ የመሰነድና የማስቀመጥ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ሌላኛው ቁልፍ ንግግር አቅራቢ በዲላ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር አብዱ መሐመድ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የገጠሟቸውን የሰላም ማጣቶችና የእርስ በእርስ ግጭቶች ብሔራዊ እርቅና የሽግግር ፍትህን ከሀገር በቀል ግጭት መፍቻ መንገዶች ጋር በማቀናጀትና በመጠቀም የፈቱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በሀገራችን በቅርቡ የተጀመሩ ሀገራዊ ምክክርና የሽግግር ፍትህ የማከናውን እንቅስቃሴዎች መጀመራቸው ትልቅ ዕድል መሆኑን በንግግራቸው የገለጹት ምሁሩ እነዚህን አሠራሮች በአግባቡ መተግበር ከተቻለ ሀገራችን ከገባችበት ቀውስና የእርስ በእርስ ግጭት ያወጣታል የሚል እምነት እንዳላቸው አውስተዋል፡፡ የኢትዮጵያ እጣ ፋንታ በሥልጣን ላይ ባሉም ሆነ በተቃዋሚ ፖለቲከኞች ብቻ መወሰን እንደሌለበት በንግግራቸው አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት ዶ/ር አብዱ የሀገሪቱን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የሚደረጉ ብሔራዊ ውይይቶችና የእርቅ መድረኮች ሁሉንም ማኅበረሰብ ማሳተፍና ነባር ሀገር በቀል እውቀቶችንም መጠቀም እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ “Amba Dagnoch: Indigenous Knowledge for Sustainable Peace Building, Dema Woreda of Amhara-Ethiopia” በሚል ርእስ የጥናት ሥራቸውን ያቀረቡት ዶ/ር ጳውሎስ አእምሮ የአምባ ዳኞች በሚል የሚጠራው ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ መንገድ በአካባቢው በስፋት ባህላዊ የግጭት መፍቻ፣ ማስታረቂያ፣ ሰላም መፍጠሪያ፣ የተበደለ የሚካስበትና የበደለ የሚቀጣበት በእጅጉ ጠቃሚ የሆነ ሥርዓት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ መሰል ሀገር በቀል ዕውቀቶች እንዳይጠፉ እንዲሁም ልምዱን በሌሎች አካባቢዎች ጭምር ለማስፋት ሊሠራ እንደሚገባ ተመራማሪው ጠቁመዋል፡፡

“Indigenous Conflict Resolution Mechanisms and Post-Crisis State Building: Insights from African States and Lessons to Ethiopia” በሚል ርእስ የምርምር ሥራቸውን ያቀረቡት ዶ/ር ይሄነው ውቡ ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ መንገዶች እስከ ታችኛው የማኅበረሰብ መዋቅር ድረስ በመድረስ አለመግባባቶችን መፍታት የሚያስችሉ መሆኑን  ተናግረዋል፡፡ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተጠቀሙባቸውን  ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ መንገዶች ያቀረቡት ዶ/ር ይሄነው ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ መንገዶችን ከመደበኛው ወይም መዋቅራዊ ከሆነው ሥርዓት ጋር በማቀናጀት መጠቀም ቢቻል ይበልጥ ውጤታማ መሆን እንደሚቻልም አመላክተዋል፡፡

በዕለቱ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በተወጣጡ ምሁራን ከዐውደ ጥናቱ መሪ ርእስ ጋር የተያያዙ 11 የምርምር ሥራዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት