የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ኅብረት ፓርላማ የ2015/16 የሥራ ዘመን መጠናቀቁን ተክትሎ ለ2017/18 ለሁለት ዓመታት የሚያገለግሉ አዲስ የተማሪዎች ኅብረት ፓርላማ ሥራ አስፈፃሚ አባላት ምርጫ ሰኔ 18/2016 ዓ.ም ተጠናቋል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የተማሪዎች ኅብረት ፓርላማ ምርጫ በዚህ መልኩ መካሄዱ ተማሪዎች በቀጣይ ወደ ሥራ ዓለም ሲቀላቀሉ ጥሩ ልምድ የሚያገኙበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የአገልግሎት ጊዜያቸውን ላጠናቀቁ ለቀድሞ ፓርላማ አባላት ምስጋና ያቀረቡት ዶ/ር ዳምጠው አዲስ ለተመረጡ አባላትና ሥራ አስፈፃሚዎችም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች አገልግሎት ም/ዳይሬክተር አቶ ካፒታ ዋልጬ በበኩላቸው የተማሪዎች ኅብረት ፓርላማ ምርጫ በየሁለት ዓመት የሚካሄድ ሲሆን በምርጫው የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ሁለት ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑና አማካይ ውጤታቸው ከ2.75 በላይ የሆኑ እንዲሁም በዲሲፕሊን ያልተከሰሱ፣ በሐይማኖት፣ በብሔር፣ በቋንቋ ልዩነት የማይፈጥሩና አብሮነትን የሚደግፉ መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

በተደረገው ምርጫ ተማሪ ሶፎኒያስ ፈንቴ የኅብረቱ ፕሬዝደንት፣ ተማሪ አፀደ ጌትነት ም/ፕሬዝደንት፣ ተማሪ ብሩክቲ ተክሉ ፀሐፊ፣ ተማሪ ጽዮን ፍቃደ ዋና ኦዲተር፣ ተማሪ ቤተልሔም ክንዴ ም/ኦዲተር፣ ተማሪ ሳሙኤል ማስረሻ ኦዲተር ሆነው ተመርጠዋል፡፡ እንዲሁም ተማሪ ሶፎኒያስ መብራቴ ዋና አፈ ጉባዔ እና ተማሪ ፋኖስ ጀግኔ ም/አፈ ጉባዔ ሆነው ተመርጠዋል፡፡

የኤሌክትሪካልና ኮምፕዩተር ምኅንድስና የ3ኛ ዓመት ተማሪ የሆነው አዲሱ የተማሪዎች ኅብረት ፓርላማ ፕሬዝደንት ተማሪ ሶፎኒያስ ፈንቴ ከምርጫው በኋላ በሰጠው አስተያየት በምርጫው በማሸነፉ መደሰቱን ገልጾ የተጣለበትን ኃላፊነት በቁርጠኝነት ለመወጣት ቃል ገብቷል፡፡

በፕሮግራሙ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ፣ የውኃ ቴክኖሎጂ ኢንሲቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ቦጋለ ገ/ማርያም፣ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር መስፍን መንዛ፣ የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ም/ዲን ዶ/ር ዮሐንስ ማሬ፣ የዩኒቨርሲቲው ሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ዳይሬክተር ወ/ሪት ሠናይት ሳህሌ፣ የተማሪዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ አየልኝ ጎታን ጨምሮ የአምስቱም ካምፓሶች የተማሪዎች ኅብረት ጽ/ቤት አስተባባሪዎች እንዲሁም የአዲሱ ተማሪዎች ኅብረት ፓርላማ አባላት ተገኝተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት