አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሳውላ ካምፓስ በመደበኛና በሳምንት መጨረሻ ያስተማራቸውን 338 የመጀመሪያና የ2 ዲግሪ ተማሪዎች ሰኔ 26/2016 ዓ/ም ለ7 ጊዜ አስመርቋል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የአካዳሚክ ጉዳዮች ዋና ሥራ አስፈጻሚና የዕለቱ የክብር እንግዳ ኤባ ሚጀና (ዶ/ር) ለተመራቂ ተማሪዎች የሥራ መመሪያ ባስተለላፉበት ወቅት እንደተናገሩት አንድ ሀገር በትክክል እንዲያድግ ከተፈለገ ጥራት ያለው ትምህርት ለዜጎች ማቅረብ አስፈላጊ ሲሆን ከኋላ ቀርነትና ከድህነት በመላቀቅ ያደጉ ሀገራት ከደረሱበት የእድገት ደረጃ ለመድረስ የትምህርት አስፈላጊነት ለጥያቄ የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም፡፡ በመሆኑም የዘመኑን ዕውቀት ተጠቅሞ ቴክኖሎጂን መፍጠር፣ ማሻሻል ወይም ማለማመድ ወሳኝ ነው ያሉት ዶ/ር ኤባ ሀገራችን ኢትዮጵያ ትምህርትን ለማሻሻል በተለያዩ ደረጃዎች ፓሊሲዎችን ከማሻሻል እና አዳዲስ የአሠራር ሥርዓቶችን በመዘረጋት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራበት ይገኛል ብለዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ኤባ ተቋማትን በትኩረትና በተልእኮ በመለየት፣ ጥራትና አግባብነትን የጠበቀ ትምህርት እንዲሰጥ ማድረግና አዳዲስ ሃሳቦችን ማፍለቅና መተግበር እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መልካም አርአያ የሚሆኑ ዜጎችን ማፍሪያ፣ የዲሞክሪሲያዊ አስተሳሰቦችና ቴክኖሎጂዎች ማፍለቅያ፣ የባህላዊ እሴቶቻችን መጎልበቻ፣ የሕዝቦች የመተሳሰብ፣ የመቻቻልና የአብሮነት ባህል መቀመሪያ ማዕከላት ሆነው እንዲሠሩ ይጠበቃል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዳምጠው ዳርዛ (ዶ/ር) የተማረ ማኅበረሰብን በማበራከት ዘላቂ እድገትን ለማረጋገጥ በሀገራችን የትምህርት ዘርፍ አሁን ላይ ለትምህርት ጥራትና አግባብነት ልዩ ትኩረት በመስጠት ሰፊ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ በአዲሱ የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ ጥናት መሠረት ከ2015 የትምህርት ዘመን ጀምሮ የሚመረቁ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች ሀገር አቀፍ የመውጫ ፈተና እየወሰዱ እንደሚመረቁ ተናግረው ለምረቃ የበቁ ተማሪዎችም የመውጫ ፈተና ያለፉ ናቸው ብለዋል፡፡ የማለፊያ ውጤት ያላመጡ ተማሪዎችም በቀጣይ ስድስት ወራት ውስጥ በድጋሚ እንደሚወስዱ ገልጸው በትዕግሥት እንዲጠባበቁ አስስበዋል፡፡

በም/ፕሬዝደንት ማዕረግ የሳውላ ካምፓስ ኃላፊ አቶ ገ/መድኅን ጫሜኖ በበኩላቸው በካምፓሱ በምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ረገድ ፈጣን የማኅበረሰብ ለውጥ ሊያመጡ በሚችሉ ዘርፎች፡- በግብርና፣ ጤና፣ ትምህርት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና በሌሎችም አካባቢውን የበለጠ ለመጥቀም ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ አክለውም የካምፓሱ መምህራንና ሠራተኞች ተማሪዎች ብቁ እንዲሆኑ ባደረጉት ጥረት በዚህ ዓመት የመውጫ ፈተና ከተፈተኑ ተማሪዎች መካከል 99 ከመቶው ከፍተኛ ውጤት እንዲሁም አምስት ትምህርት ክፍሎች መቶ በመቶ ተማሪዎችን በማሳለፍ አመርቂ ውጤት ማስመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሬጅስትራርና አሉምናይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ማሌቦ ማንቻ (ዶ/ር) የተመራቂዎችን አጠቃላይ መረጃ ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው በ2016 የትምህርት ዘመን ለ37 ዙር የሚያስመርቅ ሲሆን በሳውላ ካምፓስ ደረጃ ለ7 ጊዜ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ካምፓሱ በ18 የትምህርት ፕሮግራሞች በመደበኛና በሳምንት መጨረሻ ያስተማራቸውን 338 የቅድመ እና ድኅረ ምረቃ ተማሪዎች ለምረቃ አብቅቷል፡፡ ካምፓሱ በእስከአሁን ቆይታው 1,694 ተማሪዎችን ማስመረቁን ዶ/ር ማሌቦ ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዓለማየሁ ጩፋሞ (ዶ/ር) ተማሪዎች ያገኙት የትምህርት ውጤት ብቁ የሚያደርጋቸው መሆኑን ገልጸው መመረቃቸውን አብስረዋል፡፡

ከዕለቱ ምሩቃን መካከል ተማሪ ላምሮት ታደሰ 3.96፣ ታምራት ኢያሱ 3.83 እና  የማነ ኡርጌሳ 3.81 ውጤት በማስመዝገብ የወርቅ ሜዳሊያ ሲበረከትላቸው ተማሪ ላምሮት ታደሰ 3.96፣ ነፃነት ታደሰ 3.64 እና ማሕሌት ዘላለም 3.16 በማስመዝገብ ከሴት ተማሪዎች ልዩ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ተማሪዎች (አሉምናይ) ማኅበር ጸሐፊ ጋዜጠኛ ሣልሳዊት ባይነሳኝ ተመራቂ ተማሪዎች የማኅበሩ አባል እንዲሆኑ በመጋበዝ በመድረኩ ወላጅ ላልመጣላቸው ሦስት ተማሪዎች ወደየአካባቢያቸው የሚደርሱበት የመጓጓዣ ወጪ በሳውላ ከተማ አስተዳደር እንዲሸፈን እንዲሁም በአቅም ማነስ ምክንያት የመመረቂያ አልባሳት መግዛት ላልቻሉ ሴት ተመራቂ ተማሪዎች በክልሉ ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ጽ/ቤት በኩል የምረቃ ልብስ ማግኘት እንዲችሉ አድርጋለች፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት