Print

በዩኒቨርሲቲው ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የምርምር ዳይሬክቶሬትና በውሃ ሀብት ምርምር ማዕከል ዳይሬክቶሬት ትብብር 15ኛው ዘላቂ የውሃ ሀብት አስተዳደርና አጠቃቀም ሲምፖዚዬም ከሰኔ 26 እስከ 27/2007 /ም ተካሂዷል፡፡

ሲምፖዚዬሙ በዘላቂ የውሃ ሃብት አስተዳደርና አጠቃቀም ዙሪያ ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎች እና ባለድርሻ አካላት የጋራ መድረክ በመፍጠር የምርምር ውጤቶችን እንዲያቀርቡና የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን እንዲለዋወጡ ለማድረግ ያለመ መሆኑን በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ኢንሲትቲዩት የውሃ ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር መኮንን አያና ተናግረዋል፡፡ ለአገር ልማት አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉ በርካታ የጥናትና ምርምር ውጤቶች የሚቀርቡበት መድረክ በመሆኑ በውሃ ሃብት ዙሪያ ለፖሊሲ አውጭዎች ግብዓት ሊሆን የሚችል መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ በመክፈቻ ንግግራቸው ኢትዮጵያ በውሃ ሀብት ያላትን ከፍተኛ አቅም በአግባቡ ለመጠቀም እንዳትችል በመስኩ የሚታየው የባለሙያና የፋይናንስ አቅም ውስንነት ድርሻው የጎላ ነው ብለዋል፡፡የውሃ ሀብት አስተዳደርና አጠቃቀም በሳይንሳዊ የጥናትና ምርምር ሥራዎች መደገፍ እንደሚገባው የገለፁት ፕሬዝዳንቱ ዩኒቨርሲቲው በግንባር ቀደምነት ባለሙያዎችን በማሰልጠን በዘርፉ የሚታየውን ውስንነት ለመቅረፍ የራሱን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

በኢፌዴሪ የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የምርምር ዳይሬክተር አቶ አቢቲ ጌታነህ በመስኖ ልማት ፕሮጀክት፣በሰው ኃይል ስልጠና፣ በምርምር እና በሌሎችም ተያያዥ ዘርፎች በሚኒስቴር መ/ቤቱ በኩል የታቀዱ ሥራዎችንና የዩኒቨርሲቲዎችን ሚና አስመልክተው ለተሳታፊዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን በመስኖ ልማት ሀገራችን ካላት አቅም ከ40-50 በመቶ መጠቀም የተቻለ ሲሆን በኤሌክትሪክ ኃይል ከውሃ ፣ ከነፋስና ከጂኦተርማል ኃይል እንዳላት ከሚገመተው 45 ሺ ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም 10ሺ የሚሆነውን ለማሳካት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን በዘርፉ ባለሙያዎችን በብዛትና በጥራት በማፍራትና በጥናትና ምርምር የተሻለ ሥራ እንደሚሠሩ ጠቁመዋል፡፡

በሲምፖዚዬሙ ከተለያዩ ተቋማት በመጡ ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች 62 የጥናትና ምርምር ጽሑፎች ተመርጠው 28ቱ በመድረክና 11 ጥናቶች በፖስተር ቀርበዋል፡፡ በተጨማሪም ኔዘርላንድ ከሚገኘው ዋግናይን ዩኒቨርሲቲ የመጡትና በውሃ ሃብት ዘርፍ የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸው ፕሮፌሰር ሄንክ ሪትማን ‹‹በፍሳሽ አወጋገድ ዙሪያ የተዘነጉ እውነታዎች ›› በሚል ርዕስ ያቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ የፍሳሽ አወጋገድ ምንነት፣ ዓላማና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ዳሷል፡፡

በሲምፖዚዬሙ የዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መምህራንና ኃላፊዎች፣ ዳይሬክተሮች፣ ከውሃ ሀብት ሚኒስቴር፣ ከተለያዩ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎችና አጋር ተቋማት በአጠቃላይ 120 ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡ በማጠቃለያው የጥናትና ምርምር ጽሑፍ ላቀረቡ ባለሙያዎችና ለሲምፖዚዬሙ ስኬት ጉልህ ድርሻ ለነበራቸው አካላት በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገ//ፕሬዝዳንት አማካኝነት የምስጋና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል፡፡