ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ አካባቢ በዩኒቨርሲቲያችን ዋናው ግቢ በሁለት ተማሪዎች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት የሌሎችም ተማሪዎች የቅሬታ ምንጭ በመሆኑ ጉዳዩ በዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች፣ በአርባ ምንጭ ከተማ የሃይማኖት ፎረም ተወካይ አባቶች፣ በአገር ሽማግሌዎች ተወካዮች፣ ከተማሪዎች በተመረጡ ተወካይ ተማሪዎች እንዲሁም
ከከተማውና ከዙኑ አስተዳደር ከተወጣጡ የሠላም እሴት ግንባታ ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ሁሉ ጋር በጋራ በተደረገው ቀጣይነት ያለው ጥረት አለመግባባቱ በውይይት ብቻ ሙሉ በሙሉ ሊፈታ ችሏል፡፡
ታህሳስ 14/2011 ዓ/ም በዩኒቨርሲቲው ሴኔት አዳራሽ በተካሄደው የውይይቱ የመጨረሻ ክፍል ተማሪዎች ወጣትነት በስሜታዊነትና በኃይለኝነት ባህርይ ሊገለፅ የመፈለግ ጎትጓችነት የሚጎላበት የዕድሜያቸው ክፍል መሆኑን በመረዳት ከፍተኛ የሆነ ትዕግስት የመላበስ፣ የመረዳዳት፣ የመተሳሰብ፣ የወንድማማችነትና የእህትማማችነት፣ እርስ በእርስ በመተራረም የመቻቻል ባህል የማጎልበት እንዲሁም ከሁሉም በላይ እንደ ሠርገኛ ጤፍ ሊለይ የማይችለውን፣ በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሌሎችም ምክንያቶች ለዘመናት ያልተበገረውን ኢትዮጵያዊ ማንነት የመገንባትና የበለጠ የማጎልበት ኃላፊነት የተጣለባቸው በመሆኑ በትናንሽ ጉዳዮች ከመቃቃር ይልቅ ለአገራዊ አንድነትና እየተካሄደላለው አገራዊ ለውጥ ስኬት አጋሪነታቸውን ሊያሳዩ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም እንደ አገር ለውጡን ለመቀልበስ እየተሞከረ ያለውን ሁኔታ በመገንዘብ ተማሪዎችን ለፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች መጠቀሚያ ለማድረግ ከሚፈልጉ ግለሰቦችና ቡድኖች አጀንዳ አራማጅነት እንዲታቀቡና እንዲጠነቀቁ ይህም ለአገራቸው ደህንነትና ሠላም የሚያበረክተው አስተዋፅዖ ከፍተኛ ነው ተብሏል፡፡
አንዳንድ የታዩ ግድፈቶች በሁሉም ዘርፎች ማስተካከያ ሊደረግባቸው እንደሚገባ ታምኖበት ተማሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደርና ሌሎችም የሚመለካታቸው ባለድርሻዎች ኃላፊነት በመውሰድ ሊሠሩ ይገባል፡፡
በጨረሻም ከሁሉም በላይ ለዩኒቨርሲቲያችን ተማሪዎች የተፈጠረውን አለመግባባት በሠላማዊ መንገድ በውይይት የመፍታት ዘመናዊና ምሁራዊ ባህል በማንፀባረቅ እንዲሁም የአገራችንን ትልቅ ሀብት የሆነውን ታላላቆችን የማክበርና የመስማት ኢትዮጵያዊ ባህል ህያው በማድረግ ለተቋማችንና ሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎችና ተቋማት አርኣያነት ያለውን ተግባር የፈፀማችሁ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲያችን ልባዊ ምስጋና ያቀርባል፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት