የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ረንረስ /RUNRES/ ፕሮጀክት ከ‹‹International Institute of Tropical Agriculture››፣  ‹‹University of Kwazulu-Natal››፣ ‹‹ETH-Zurich›› እና ከስዊዘርላንድ ልማት ተራድዖ ድርጅት (SDC)  ጋር  በመተባበር ከተማና ገጠርን በንጥረ ነገር ማስተሳሰር ላይ በሚሠራው ፕሮጀክት የ4ዓመት የፕሮጀክት ዕቅድ አፈጻጸም ዙሪያ የምክክር ወርክሾፕ ከየካቲት 6-10/2015 ዓ/ም በአርባ ምንጭ ፓራዳይዝ ሎጅ አካሂዷል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የፕሮጀክቱ ዓላማ ከተማ ላይ የሚመነጨውን ቆሻሻ በተፈጥሮ ማዳበሪያ /Compost/ መልክ ወደአርሶ አደሩ ማቅረብና ተጠቃሚዎች ሙዝን በተለያየ መልኩ ማግኘት እንዲችሉ የሙዝ ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂዎችን ማዳበር ነው፡፡ በዚህም ከተማው ገጠሩን እንዲሁም ገጠሩ ከተማውን መመገብ በሚችልበት ሂደት ዑደታዊ /Circular/ ኢኮኖሚን በመመሥረት የምግብ ዋስትናን እና ጽዱ የሆነ ከተማን መፍጠር ግቡ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ረንረስ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ዓባይነህ ፈይሶ ገልጸዋል፡፡ የሙዝ እሴቶችን የሚጨምሩ ቴክኖሎጂዎች ተገጥመው ሥራ የጀመሩ መሆኑንና ከአርባ ምንጭ ከተማ ደረቅ ቆሻሻን ሰብስቦ አክሞ ለመጠቀም ያስችል ዘንድ ቆሻሻን ለሚሰበስቡ ማኅበራት ሁለት ተሽከርካሪዎች እና የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማብላያ ማሽን መገዛቱን አቶ ዓባይነህ ጠቁመዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በበኩላቸው የፕሮጀክቱ ትስስር ዓላማ ለምርትና ምርታማነት የሚጠቅሙ ግብዓቶችን በማቅረብና በማሻሻል የሰውን ጤና መጠበቅ፣ ኢኮኖሚን ማበልጸግ እና በዘርፉ ለተሠማሩ አርሶ አደሮች ሀብት መጨመር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እንደ ተ/ፕ/ በኃይሉ የአካባቢ ንጽሕናን ለመጠበቅ ቆሻሻን በመሰብሰብ በሳይንሳዊ መንገድ ለይተውና አብላልተው የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ቀልዝ) ለሚሠሩ ማኅበራት የሚሸጋገር ሲሆን ማኅበራቱ የሚያዘጋጁት የተፈጥሮ ማዳበሪያ በንጥረ ነገር ይዘት አትክልቶችን የማይጎዳ መሆኑን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በመለየት ለአምራቾች ማከፋፈልና በአርሶ አደሮች ዘንድ ትስስር መፍጠርንም ያካትታል፡፡

ለሥራው የተደራጁ ማኅበራት ጥሩ ውጤት እያሳዩ መሆኑን ም/ፕሬዝደንቱ ገልጸው በዩኒቨርሲቲው በኩል ማኅበራቱ ሕጋዊ መንገድን ተከትለው እንዲሄዱ የማድረግ፣ የተገዙ ዕቃዎችን በሕጋዊ መንገድ ለማኅበራቱ የማስተላለፍና ችግሮች ቢከሰቱ ንብረቶቹን በሕጋዊ መንገድ ወደዩኒቨርሲቲው የማስመለስ፣ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በውይይት እንዲፈቱ የማድረግ እና የፕሮጀክቱን ባለሙያዎች የመደገፍ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በፕሮግራሙ በኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና ደቡብ አፍሪካ በዘርፉ የተከናወኑ ተግባራትን ገምግሞ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በመቅረፍ መልካም ተሞክሮዎችን በማጎልበትና በማስፋት ወደ2ው ዙር የፕሮጀክት ሥራ ማሸጋገር እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት