ወ/ሮ ምሥራቅ ምስክር ከአባታቸው አቶ ምስክር ምንዳ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ካቡሬ ኮሎ በአርባ ምንጭ ከተማ ወዜ ቀበሌ ጥቅምት 12/1985 ዓ/ም ተወለዱ፡፡ ወ/ሮ ምሥራቅ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአርባ ምንጭ ሙሉ 1 ደረጃ ት/ቤት እና የ2ደረጃ ትምህርታቸውን በአርባ ምንጭ አጠቃላይ 2 ደረጃ ት/ቤት ያጠናቀቁ ሲሆን በአርባ ምንጭ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለ3 ዓመት ሠልጥነው ጥቅምት 24/2005 ዓ/ም በፋርማሲ ቴክኒሺያንነት በደረጃ 4 ተመርቀዋል፡፡

ወ/ሮ ምሥራቅ ከጥቅምት 1/2006 - ጥቅምት 30/2007 ዓ/ም በቋሚ ቅጥር በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች አገልግሎት አበጣሪ ሠራተኛ፣ በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የተማሪዎች አገልግሎት ክሊኒክ ከኅዳር 1/2007 - ጥር 30/2008 ዓ/ም የሕሙማን ካርድ ክፍል ሠራተኛ፣ ከየካቲት 1/2008 - ሰኔ 30/2013 ዓ/ም ጁኒዬር ፋርማሲስትና ከሐምሌ 1/2013 ዓ/ም ጀምሮ ሕይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ ፋርማሲ ቴክኒሺያን በመሆን ተቋሙን ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡

ወ/ሮ ምሥራቅ ባለትዳርና የ3 ልጆች እናት ሲሆኑ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው የካቲት 08/2015 ዓ/ም በተወለዱ በ30 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በወ/ሮ ምሥራቅ ምስክር ኅልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን እየገለጸ ለሟች ቤተሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶች፣ ጓደኞችና የሥራ ባልደረቦች እንዲሁም ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ መጽናናትን ይመኛል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት