ተማሪ አየለ አካሉ ከእናቱ ወ/ሮ ሙሉነሽ መርሻ እና ከአባቱ ከአቶ አካሉ ወልደኪዳን በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሰሜን ሸዋ ዞን ሞጃና ወደራ ወረዳ ሰላ ድንጋይ ፍላገነት ቀበሌ በ1991 ዓ/ም ተወለደ፡፡ ተማሪ አየለ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በወረዳው እምቧይ ባድ ሙሉ 1 ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የ2 ደረጃ ትምህርቱን በሳሲት አጠቃላይ 2 ደረጃ ት/ቤት እንዲሁም የመሰናዶ ትምህርቱን በሰላ ድንጋይ አጠቃላይ 2 ደረጃና መሰናዶ ት/ቤት ተከታትሏል፡፡

ተማሪ አየለ በ2012 ዓ/ም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተመድቦ በግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ‹‹Rural Development and Agricultural Extension›› የትምህርት ክፍል በአግሮ ኢኮኖሚ ትምህርት መስክ ትምህርቱን በመከታተል ላይ ነበር፡፡ የ3 ዓመት ተማሪ የነበረው ተማሪ አየለ በ2015 ዓ/ም መጨረሻ ከሚመረቁ ተማሪዎች መካከል አንዱ ነበር፡፡

ተማሪ አየለ የካቲት 7/2015 ዓ/ም በጧት የነበረውን ገለጻ በማጠናቀቅ ምሳውን ተመግቦ ወደዶርሚተሪው ተመልሶ መኝታው ላይ ዕረፍት ላይ ባለበት ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ከዚህ በፊትም በተለይ በፈተና ጊዜያት በሚጥለው ሕመም ዓይነት ከተኛበት በድንገት ተዝለፍልፎ በመውደቁ የዶርም ጓደኞቹ በአቅራቢያ ወዳላው ነጭ ሣር ሆስፒታል በፍጥነት በማድረስ ሕይወቱን ለማዳን ጥረት ቢደረግም የተማሪው ሕይወት ማለፉ በሆስፒታሉ ተረጋግጧል፡፡ ቀጥሎም የተማሪው አስከሬን አርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ተልኮ በተደረገው የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራ የሞቱ መንስዔ የምግብ ችግር አለመሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን በመቀጠልም በዳግማዊ ሚኒልክ ሆስፒታል የአስከሬን ምርመራ ተደርጎ  ውጤቱ በቀጣይ እንደሚገለጽ በተነገረው መሠረት የተማሪው አስክሬን ወደቤተሰቦቹ ተሸኝቷል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተማሪ አየለ አካሉ ኅልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን እየገለጸ ለሟች ቤተሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶችና ጓደኞች እንዲሁም ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ መጽናናትን ይመኛል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት