አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከ‹‹GIZ›› ግብረ ሠናይ ድርጅት ጋር በመተባበር ‹‹Women in Agriculture and Rural Livelihoods›› በሚል ርዕስ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ተመራማሪዎችና መምህራን በተገኙበት የካቲት 6/2015 ዓ/ም ወርክሾፕ አካሂዷል፡፡ በወርክሾፑ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ  እንደገለጹት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሴቶችን የሚጠቅሙና አኗኗራቸውን የሚያሻሽሉ የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየሠራ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው የፀሐይ ኃይልን በመጠቀም የጤና ተቋማትንና ት/ቤቶችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረጉ፣ በእንሰት ተክል ዙሪያ እየተከናወኑ የሚገኙ የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎችና የተለያዩ የንጹሕ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ከዚህ አንጻር ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡ GIZ በግብርናው መስክ የሴቶችን ሚና ለማጎልበትና አኗኗር ለማሻሻል እያከናወነ የሚገኘው ፕሮጀክት ፋይዳው ሀገራዊ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ለፕሮጀክቱ ስኬት የሚጠበቅበትን ለመወጣት ዝግጁ እንደሆነ ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በሀገሪቱ የግብርና ሥርዓት ውስጥ ሴቶች የሚጫወቱት ሚና ጉልህ መሆኑን ጠቅሰው በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በተለይ በታዳጊ ሀገራት የግብርናው መስክ በእጅጉ እየተጎዳ ሲሆን በዚህም ሴቶች ዋነኛ ተጎጂዎች ናቸው ብለዋል፡፡ እንደኢትዮጵያ ባሉ ኢኮኖሚያቸው በግብርና ላይ የተመሠረተ ሀገራት የዘርፉን ውጤታማነት ለማጎልበት በመስኩ የሚደረጉ ምርምሮችና በምርምር ውጤቶች ላይ በመመሥረት የሚሠሩ ሥራዎች ወሳኝ በመሆናቸው GIZ በመስኩ የጀመረው ሥራ የሚበረታታ መሆኑን ም/ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡ 

የምርምር ዳይሬክቶሬት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀብተማሪያም በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ኢንስቲትዩቶች ጋር በአቅም ግንባታ፣ በጥናትና ምርምርና በማኅበረሰብ አገልግሎት ዙሪያ በጋራ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትነት ሲመሠረት ጀምሮ ከተለያዩ የጀርመን ተቋማት ጋር በጋራ ሲሠራ መቆየቱንና ይህም ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ መሠረት መሆኑንም ዶ/ር ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ ፕ/ር ጉንሰር ስችሊ/Prof. Gunther Schlee/ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በገጠር የሚገኙ ሴቶችን አኗኗር፣ ፍላጎትና ችግሮች ለማወቅ የሚደረግ ጥናትን ያካተተ ነው ብለዋል፡፡ በፕሮጀክቱ የሴቶችን ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ ጥናቶችና የልማት ሥራዎች በኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ አማራና ሲዳማ ክልሎች ሲካሄድ መቆየቱን የገለጹት ፕ/ር ጉንሰር ወርክሾፑ በፕሮጀክቱ የተሠሩ ሥራዎችን በምሁራን በማስገምገም ቀጣይ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ ‹‹GIZ›› ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በተለያዩ መስኮች በትብብር እየሠራ ሲሆን በዚህኛው ፕሮጀክትም ዩኒቨርሲቲውና የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ 

በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ተመራማሪና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል አንትሮፖሎጂ ት/ክፍል መምህርት ዶ/ር ትርሲት ሣህለድንግል የፌሚኒዝም ምርምር ዘዴ ላይ ጽሑፍ ሲያቀርቡ እንደተናገሩት ፌሚኒዝም በሁሉም የሕይወት ዘርፍ የሴቶችን እኩልነት እና ፍትሕን መፈለግን መነሻ በማድረግ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ግላዊ እና ማኅበራዊ የጾታ እኩልነትን ለመተንተን፣ ለመመሥረትና ለማስፈን የጋራ ግብ ያላቸው ሰፊ አስተሳሰቦች እና ማኅበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን ያካትታል፡፡

አክለውም የፌሚኒስት ጥናት በዓለም ላይ ለውጥን ለማምጣት እና የሥርዓተ ጾታ አለመመጣጠንን ለማስቀረት የሴቶችን ልምድ፣ ፍላጎቶችና የማኅበራዊ ዓለም ግንዛቤ ከግምት ከሚያስገባው ዕይታ መነሻነት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ትርሲት ገለጻ የፌሚኒስት ጥናት ስለሴቶች ሁሉንም ነገር መናገር ባይችልም በሴቶች ልምድ እውነታ ላይ የተመሠረተ አዲስ ዕውቀት መስጠት እና በማኅበራዊ ዓለም ውስጥ መዋቅራዊ ለውጦችን በንቃት ማሳየት ይችላል።

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የባዮቴክኖሎጂ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ በእንሰት ተክልና የምርት ሂደት ላይ ‹‹Easing the Lives of Rural Women: Enset Processing Machine in Use›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ እንሰት በደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብና መካከለኛው የሀገሪቱ ክፍል ለሚኖረው ከ20 ሚሊየን በላይ የሚሆን ሕዝብ ዋነኛ የምግብ ምንጭ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኋላ ቀር የእንሰት አመራረትና የማብላላት ሂደትን ለማስቀረት ጥናቶችን ማካሄዱን እንዲሁም ሂደቱን የሚያዘምኑ ቴክኖሎጂዎችን ፈጥሮ ማስተዋወቁን  ይህም የምርት ጥራት መሻሻል፣ ብክነት መቀነስና በከፍተኛ ሁኔታ የሴቶችን ጉልበት መቆጠብ ማስቻሉንም አብራርተዋል፡፡ 

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት