የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂ ምርምር ማዕከል ከሳሃይ ሶላር አሶሴሽን/Sahay Solar Association/ ጋር በመተባበር ከስዊዘርላንድ፣ ከጋሞና ጎፋ ዞኖች እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲው ለተወጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎችና ተማሪዎች የፀሐይ ኃይልን ለመብራትና ለተለያየ አገልግሎት መጠቀም በሚያስችሉ ዘዴዎች /Photovoltaic Technology/ ዙሪያ ከጥር  30 - የካቲት 9/2015 ዓ/ም  ለተከታታይ 9 ቀናት የአቅም ግንባታ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ የሳሃይ ሶላር ፕሮጀክት ሲጀመር በአነስተኛ መምህራን እንደነበር አስታውሰው ፕሮጀክቱ በዘርፉ የአቅም ግንባታና የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን በስፋት ሲሠራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ በፕሮጀክቱ የሚሠሩ ሥራዎች በቅንጅት የሚሠሩ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ሙሉነህ ሥራው የማኅበረሰቡን አኗኗር የሚያሻሽል በመሆኑ የተጀመረው ሁለንተናዊ ቅንጅት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

የሳሃይ ሶላር ኢኒሼቲቭ/Sahay Solar Initiative/ መሥራችና የጀርመን ቅርንጫፍ ተወካይ ማክስ ፖል (Max Pohle) በበኩላቸው ሥልጠናው በፀሐይ ኃይል ቴክኖለጂ ዙሪያ በንድፈ ሃሳብና በተግባር የተደገፈ ክሂሎት ለማስጨበጥ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በፕሮጀክቱ አማካኝነት በጋሞና ጎፋ ዞኖች የሚገኙ የትምህርትና ጤና ተቋማትን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ያስታወሱት የቅርንጫፉ ተወካይ ሥልጠናው በቀጣይ ሥራውን ለማስቀጠል ለተያዘው ውጥን አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂ ምርምር ማዕከል ዳይሬክተርና የፕሮጀክቱ ቴክኒካል ማኔጀር አቶ ሶዴሳ ሶማ  ሥልጠናው ለ10 ጊዜ መሰጠቱንና ከስዊዘርላንድ የመጡ ተማሪዎችና ለዘርፉ ቅርበት ያላቸው ሙያተኞች መሳተፋቸውን ጠቁመዋል፡፡ ሥልጠናው የፕሮጀክቱን ዓላማ መሠረት በማድረግ በቀጣይ የማኅበረሰብ ጉድኝት ሥራዎችን ለማጠናከርና በጋሞና ጎፋ ዞኖች የሚገኙ የትምህርትና የጤና ተቋማትን የመብራት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አቅም ለመገንባት ያለመ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አውስተዋል፡፡ መንግሥት በታዳሽ ኃይል አማራጭ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሶዴሳ ይህንን ሀገራዊ ዕቅድ ከመደገፍ አንጻር በዘርፉ የሠለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ ተቋሙ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ 

ከስዊዘርላድ ሉሰርን አፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ/Lucerne University of Aplied Sciences/ የመጡት አሠልጣኝና መምህር ፕ/ር ሮጀር ቡሰር/Roger Buser/ እንደገለጹት ሥልጠናው በዋናነት ሠልጣኞች በመስኩ የቴክኖሎጂ ልውውጥና ሽግግር እንዲያደርጉና የተግባር ልምድ እንዲወስዱ የሚያስችል ነው፡፡ በሥልጠናው ሶላር ሲስተምን ዲዛይን ማድረግ፣ ማስላት፣ አስፈላጊ ቁሳቁሶችን መለየት እንዲሁም በብልሽት ጊዜ የሚደረጉ የጥገና አሠራሮች የተካተቱበት እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት በሥልጠናው ከዚህ ቀደም በንድፈ ሃሳብ ደረጃ የሚያውቋቸውን ቴክኖሎጂዎች በተግባር በማየት ሶላር ሲስተምን ዲዛይን የማድረግ እንዲሁም የመጠገን ክሂሎት ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ ከሥልጠናው ባሻገርም ከሠልጣኞች ጋር በነበረን መስተጋብር ጠቃሚ ልምዶችን ያገኘንበት ነው ብለዋል፡፡

በሥልጠናው ማብቂያ ለሠልጣኞች የምስክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት