የአርባ ምንጭ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከአሜሪካው ቴክሳስ ግብርናና ሜካኒካል ዩኒቨርሲቲ/ Texsas Agricultural & Mechanical University/ ጋር በመተባባር ‹‹Integrated Decision Support System (IDSS)›› በሚል ርዕስ ከጎረቤት ሀገራት ለመጡና ከሀገር ውስጥ ለተወጣጡ በውኃ ምኅንድስና፣ ግብርና፣ ኢኮኖሚክስ፣ አካባቢ ጥበቃና ሌሎች ዘርፎች የሚያስተምሩ መምህራንና ባለሙያዎች ከጥር 6-10/2015 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ ሥልጠናው የዘርፉ ባለሙያዎችንና ምሁራንን ከተለያዩ አዳዲስ አሠራሮች ጋር በማስተዋወቅ ራሳቸውን እንዲያበቁ የሚረዳና የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚደረግበት ነው ብለዋል፡፡  ኢትዮጵያ በየደረጃው የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በትጋት እየሠራች ትገኛለች ያሉት ዶ/ር ዓለማየሁ ይህንን ለማሳካት መሰል የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን መስጠት ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነም አመላክተዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ዓለማየሁ ገለጻ ግብርናና ውሃ የማይነጣጠሉ ዘርፎች እንደመሆናቸው የዚህ ዓይነት የቅንጅት ሥልጠናዎች ጠንካራ የሆነ የኢኮኖሚ ዘርፍ ለመገንባት ሚናቸው ከፍተኛ ነውም ብለዋል፡፡

የውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶ/ር ደመላሽ ወንድማገኘሁ በሥልጠናው ከሀገር ውስጥ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ከወላይታ ሶዶ፣ ሀዋሳ፣ ባሕር ዳር፣ መዳ ወላቡና ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ከጎረቤት ሀገራት ከሱማሊላንድ፣ ከዓለም አቀፍ የውኃ ጥበቃ ኢንስቲትዩትና ከሌሎች ተቋማት የተወጣጡ የዘርፉ ምሁራንና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል ብለዋል፡፡

ከቴክሳስ ግብርናና ሜካኒካል ዩኒቨርሲቲ የመጡት የሥልጠናው ዋና አስተባባሪና አሠልጣኝ ዶ/ር ጂያን ክላውድ /Dr. Jean Claude/ ሥልጠናው በሁለት ባዮሎጂያዊና በአንድ ኢኮኖሚያዊ ሞዴሎች ላይ መሰጠቱን ገልጸው ይህም በግብርና፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በመስኖ፣ በተመጣጠነ ምግብና በሀገሪቱ ዝቅተኛ የነፍስ ወከፍ ገቢ ላላቸው ማኅበረሰብ ክፍሎች የዕለት ገቢያቸውን ለማሻሻል እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡ አክለውም ሥልጠናው ከአርባ ምንጭና ሌሎች የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ያለንን የሁለትዮሽ ስምምነት ያጠናክራል ብለዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሃይድሮሊክስና ውኃ ሀብት ምኅንድስና መምህርና ተመራማሪ መ/ር አያልቅ በለጠ በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው ለቀጣይ የምርምርና ማስተማር ሥራዎች የሚጠቅም መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሥልጠናው መጨረሻ ለተሳታፊዎች የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት