አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከሮማንና ኃይለማርያም ፋውንዴሽን፣ ከቤልጂየሙ ኬዩሊዩቨን ዩኒቨርሲቲ/KU Leuven University/ እና ቢኦኤስ+/BOS+/ ከተሰኘ ድርጅት ጋር በመተባበር በጫሞ ሐይቅ ተፋሰስና ረግረጋማ ቦታዎችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ የተጀመረው የሙከራ /Pilot/ ፕሮጀክት አፈፃፀም ውጤታማና ለቀጣይ ሰፋፊ ሥራዎች ማሳያ ልምዶች እየተገኙበት መሆኑ ተገለጸ፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

ሐይቆችን በዘላቂነት ከአደጋ ለመታደግ ሳይንሳዊ መረጃዎች ላይ ተመሥርቶ የሚሠራ ዘላቂ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ መሥራት የግድ ነው፡፡ በዚህም መነሻነት በዩኒቨርሲቲውና በዘርፉ ምሁራን የምርምር ውጤቶችን መነሻ በማድረግ በጫሞ ሐይቅ ተፋሰስ 10 ወረዳዎች ላይ ዘላቂ የመሬትና የውሃ አያያዝ ላይ የሚሠራ ለ5 ዓመታት የሚቆይ ፕሮጀክት በቅርቡ ይፋ መሆኑ ይታወሳል፡፡ 

ከጀርመን ልማት ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የሚሠራው ይህ ፕሮጀክት የተግባር ሥራው እስኪጀመር ድረስ ለፕሮጀክቱ እንደ ሙከራ ሆኖ የሚያገለግልና በትንሽ ገንዘብና በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊሠራ የሚችል የትብብር ፕሮጀት ተቀይሶ የጫሞ ተፋሰስ አካል በሆነው የጌዣ ደን ውስጥ እንዲሁም በሐይቁ ረግረጋማ ስፍራ ላይ የመልሶ ማልማት ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ‹‹AMU-IUC›› ፕሮግራም ማኔጀርና የውሃ ስነ-ምኅዳር ተመራማሪ ዶ/ር ፋሲል እሸቱ የጌዣ ደን በጫሞ የላይኛው ተፋሰስ ውስጥ የቀረ ብቸኛው የደን ሀብት መሆኑን ጠቅሰው ከዚህ ቀደም የደኑን በፈር ዞን የመለየትና ተጨማሪ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ከ‹‹GIZ›› ጋር በመተባበር ሲሠራ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ፋሲል ገለጻ በደኑ ውስጥ ቀደም ብሎ መንገድ ለመሥራት ታስቦ ቁፋሮ በመደረጉ ምክንያት ለአፈር መሸርሸር ትልቅ ሚና የሚጫወት ጎርጅ /Gully/ ተፈጥሯል፡፡ በፕሮጀክቱ ሀገር በቀል ዕውቀትና ሳይንስን በተከተለ መልኩ በአካባቢው የሚገኙ ቁሳቁሶችን በመጠቀም ከዚህ ቀደም በ‹‹GIZ›› በተሠራ የአፈር መከላከያ ግድብ /Brush Wood Check Dam/ ላይ ስነ-ሕይወታዊ ሥራዎችን በመሥራት ቦታው እንዲያገግም ጥረቶች እየተደረጉ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር በተሠራው የመከላከያ ግድብ ላይ ማኅበረሰቡን ሊጠቅሙ የሚችሉ ለከብት መኖነት የሚያገለግሉ ተክሎች የተተከሉ ሲሆን በአዲስ ዲዛይን ተጨማሪ የአፈር መከላከያ ግድብ በመሥራት አካላዊና ስነ-ሕይወታዊ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል፡፡ በደኑ ውስጥ 2 ሄክታር በሚሆን ክፍት ቦታ ላይ ሀገር በቀል ዛፎች ተተክለው እንክብካቤ እየተደረገላቸው እንደሆነም ዶ/ር ፋሲል ገልጸዋል፡፡  

ረግረጋማ ስፍራ /Wetland/ ወደሐይቅ አላስፈላጊ ኬሚካሎች እንዲሁም ደለል እንዳይገባ በከፍተኛ ሁኔታ የሚከላከል መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ፋሲል ለዚሁ ሥራ ሠርቶ ማሳየነት 3 ሄክታር ረግረጋማ መሬት ለሌቶ ዓሳ አስጋሪዎች ማኅበርና ለ‹‹AMU-IUC›› ካርታ ተዘጋጅቶ መረከብ ተችሏል፡፡ በዚሁ ስፍራ ላይ ከዚህ ቀደም ጠፍተው የነበሩ እንደደንገል ያሉ የረግረጋማ ቦታ ተክሎችን በመትከል አስፈላጊው እንክብካቤና ጥበቃ እየተደረገ ሲሆን ቦታው ከሰው ንክኪ የጸዳ እንዲሆን በመደረጉ እንደሶኬ ያሉ ተክሎች በራሳቸው እየበቀሉ ነው፤ ይህም ቦታው በአጭር ጊዜ ውስጥ ማገገም እንደሚችል የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡

በቀጣይም ማኅበሩ በተረከበው ቦታ ላይ ወደ አካባቢው ለሚመጡ እንግዶች የሚሆን ከተፈጥሮው ጋር የሚስማማ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራ ለመገንባት እስከ 2.5 ሚሊየን ብር የሚፈጅ ግንባታ  የዲዛይን ሥራ መጠናቀቁን  ዶ/ር ፋሲል ጠቁመዋል፡፡ ሥራው ባህላዊ የዓሳ መመገቢያ ቦታ፣ ሰው ሠራሽ የዓሳ ማራቢያ ገንዳዎች እና የሶላርና ባዮጋዝ የኃይል አማራጮችን ያካተተ ሲሆን ግንባታው ተፈጥሮንና ባህልን ባገናዘበ መንገድ በቀርከሃ ግንባታ ሥራ ላይ ልምድ ባለው ኢምባር/IMBAR/ በተሰኘ ድርጅት የሚሠራ ይሆናል ብለዋል፡፡ ሥራው በቅርቡ እንደሚጀመርና ስፍራውም በዘላቂ የረግረጋማ ስፍራ አያያዝ ዙሪያ ሞዴል ሠርቶ ማሳያ ከመሆኑ ባሻገር በቀጣይ በመስኩ ለሚሠሩ ሥራዎች መነሻ ሆኖ እንደሚያገለግልም ዶ/ር ፋሲል ተናግረዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተባባሪ ፕሮፌሰር በኃይሉ መርደኪዮስ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲውና የመስኩ ምሁራን የጫሞ ሐይቅ አደጋ ላይ መሆኑን በተደጋጋሚ በተለያዩ መንገዶች ድምፃቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል፡፡ ከረዥም ጊዜና ከበርካታ ጥረቶች በኋላ በመንግሥትና ሌሎች ግብረሠናይ ድርጅቶች የሐይቁ ጉዳይ ትኩረት አግኝቶ በዩኒቨርሲቲው የተደረጉ ምርምሮች ላይ የተመሠረቱ የሐይቁን ተፋሰስና ረግረጋማ ቦታ ወደነበረበት መመለስ የሚያስችሉ ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡ ከዚህ አንጻር የሐይቁ የማጣሪያ ኩላሊት በሆነው ረግረጋማ ስፍራ ላይ የተጀመረው የሙከራ ፕሮጀክት የሚጠቀስ ሲሆን ሥራው ማኅበረሰቡን ባሳተፈና ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ የሚሠራ በመሆኑ ለቀጣይ ሥራዎች መነሻ ሆኖ የሚያገልግል እንደሆነ ም/ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡

የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በጋራ ማቀድ፣ ማልማትና መሥራት የሚለውን የማኅበረሰብ ጉድኝት ጽንሰ ሃሳብ በተግባር ያሳየ ነው ብለዋል፡፡ ከሌቶ ዓሳ አስጋሪዎች ማኅበር ጋር በጋራ ለማልማት የተሰጠውን ሦስት ሄክታር ረግረጋማ መሬት ለማልማት በሚሠራው ፕሮጀክት ዳይሬክቶሬታቸው ችግኞችን በማቅረብ የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ተክሉ በቀጣይም በቦታው ሊሠራ ለታሰበው ሥራ በሚዘጋጅ የመግባቢያ ስምምነት መሠረት ዳይሬክቶሬታቸው የበኩሉን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል፡፡  

የሌቶ ዓሳ አስጋሪዎች ማኅበር ዋና ሰብሳቢ አቶ ኩምሳሬ ኩሽሬ እንደተናገሩት ማኅበሩ በ2003 ዓ/ም በ34 አባላት የተመሠረተ ሲሆን አሁን ላይ 77 አባላት አሉት፡፡ ማኅበሩ ዓሳ ከማስገር ባሻገር ወደ ስፍራው ለሚመጡ እንግዶች የምግብ አገልግሎት  የሚያቀርብ ሲሆን ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመሆን በቦታው ላይ ለተተከሉ የረግረጋማ ቦታ ተክሎች አስፈላጊውን ጥበቃና ክትትል እያደረጉ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ በፕሮጀክቱ በሚሠሩ ሥራዎች ላይ የሚሰጣቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ማኅበራቸው ዝግጁ መሆኑንም ሰብሳቢው ተናግረዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት