አቶ መንገሻ መንደዶ ከአባታቸው መንደዶ መጃ እና ከእናታቸው ዋንታሌ አካንቶ በቀድሞ በሰሜን ኦሞ ክፍለ ሀገር ቦሎሶ ሶሬ አውራጃ መጋቢት 28/1958 ዓ.ም ተወለዱ፡፡

አቶ መንገሻ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ የ1 ደረጃ ትምህርታቸውን አንጭቾ 1 ደረጃ ት/ቤት እና የ2 ደረጃ ትምህርታቸውን በአርባ ምንጭ አጠቃላይ 2ደረጃ ት/ቤት በማጠናቀቅ ከአርባ ምንጭ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በአውቶሞቲቭ ኢንጅነሪንግ ሰርቪስና መካኒክስ ሙያ በደረጃ III ሠልጥነዋል፡፡

አቶ መንገሻ ከ1977 – 1979 ዓ/ም በብሄራዊ ውትድርና ሀገራቸውን ሲያገለግሉ ቆይተው ከኅዳር 06/1979 ዓ.ም  ጀምሮ ዪኒቨርሲቲውን በመቀላቀል  እስከ ግንቦት 30 1985 ዓ.ም ድረስ የጠቅላላ አገልግሎት ዋና ክፍል የጽሕፈት ሥራ ረዳት በመሆን፣ ከሰኔ 01/1985 ዓ.ም  እስከ ነሐሴ 21/1988 ዓ.ም የጠቅላላ አገልግሎት ዋና ክፍል ተጠባባቂ የተሽከርካሪዎች ስምሪት ኃላፊ በመሆን፣ ከነሐሴ 22/1988 ዓ.ም እስከ የካቲት 30/1991 ዓ.ም  የመለስተኛ መኪና ሾፌር በመሆን እንዲሁም  ከመጋቢት 01/1991 ዓ.ም እስከ ሐምሌ 30/2006 ዓ.ም በሾፌርነት ዩኒቨርሲቲውን አገልግለዋል፡፡

አቶ መንገሻ ባለትዳርና የአራት ወንድ ልጆችና የአራት ሴት ልጆች አባት ሲሆኑ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ57 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በአቶ መንገሻ ኅልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን እየገለጸ ለሟች ቤተሰቦች፣ የሥራ ባልደረቦችና ጓደኞች እንዲሁም ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ መጽናናትን ይመኛል፡፡

 

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት.