የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት በ2014 የትምህርት ዘመን የ12 ክፍል ብሔራዊ ፈተና ወስደው ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች የካቲት 16/2015 ዓ/ም የሽልማት መርሃ ግብር አካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

በት/ቤቱ በ2014 የትምህርት ዘመን ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት 50 ከመቶና ከዚያ በላይ ያስመዘገቡት 31 ተማሪዎች ሲሆኑ 5 ተማሪዎች ከ500  ነጥብ በላይ ማምጣታቸውን የት/ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሥላስ ጎዳና ገልጸዋል፡፡ በተገኘው ውጤትም ለተማሪዎች፣ ለተማሪ ወላጆች፣ ለመምህራንና ለአመራሮች የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የ2014 ዓ/ም የ12 ክፍል ብሔራዊ ፈተና ሥርዓት ጥራቱን የጠበቀና ከኩረጃ ነጻ መሆኑን ጠቅሰው በዚህ ሂደት አልፈው ወደ ዩኒቨርሲቲዎች የሚቀላቀሉ ተማሪዎች በስኬት እንደሚያጠናቅቁ አምናለሁ ብለዋል፡፡ የተመዘገበው ውጤት የዩኒቨርሲቲው ኮሚዩኒቲ ት/ቤት ተማሪዎች በቀጣይ የተሻለ እንዲሠሩና መቶ በመቶ ስኬታማ ለመሆን ት/ቤቱ ድክመቶችን ለይቶ በአግባቡ እንዲሠራ ፍንጭ የሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በበኩላቸው የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እንደሀገር የተወሰደው የትምህርት ዘርፍ የለውጥ ሥራ ለቤተሰብ፣ ለተማሪ ብሎም ለፈተና ተማሪዎችን ተቀብለው ላስተናገዱ ተቋማት ፈታኝ ወቅት እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ም/ፕሬዝደንቱ በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ተፈትነው በዞኑና በከተማ አስተዳደሩ ካሉ ት/ቤቶች ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገባቸው ተማሪዎችን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡ የተማሪዎቹ ውጤት አስደሳች ቢሆንም በሌላ በኩል ለበለጠ ሥራ በቁጭት የሚያነሳሳ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የዩኒቨርሲቲው ኮሚዩኒቲ ት/ቤት ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እንደገለጹት በት/ቤቱ በ2014 የትምህርት ዘመን 136 ተማሪዎች ለ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና የተቀመጡ ሲሆን በተፈጥሮ ሳይንስ ከተፈተኑ 81 ተማሪዎች 29ኙ እንዲሁም በማኅበራዊ ሳይንስ ከተፈተኑ 55 ተማሪዎች መካከል 2ቱ 50 ከመቶና ከዚያ በላይ ውጤት አስመዝግበዋል፡፡ አንድ ተማሪ 629 ነጥብ ያመጣ ሲሆን ይህም እንደ ሀገር 3ኛው ከፍተኛ ውጤት ሆኖ ተመዝግቧል ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ከተማ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ ተወካይ አቶ ካሡ አሳምነው እንደገለጹት በ2014 የትምህርት ዘመን በከተማው ከሚገኙ ት/ቤቶች የ12 ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከወሰዱ 1,600 ተማሪዎች መካከል ጋሞ ዞንን ጨምሮ 125 ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ያመጡ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 31ዱ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒቲ ት/ቤት ተማሪዎች ናቸው፡፡ ጽ/ቤቱ የተለያዩ የትምህርት ባለሙያዎችን እየላከ ድጋፍና ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን ያስታወሱት አቶ ካሡ ለወደፊቱ ለበለጠ ውጤት በትብብር እንሠራለን ብለዋል፡፡

የ12 ክፍል ብሔራዊ ፈተና ወስዶ 629 ነጥብ ያስመዘገበው ተማሪ ቢንያም ጩንጬ ፈተናውን በተረጋጋ ስሜት መፈተኑንና ባገኘው ውጤትም ሆነ በሽልማቱ መደሰቱን ተናግሯል፡፡ ተማሪዎች ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ ጊዜያቸውን ከሚሻሙ የተለያዩ ነገሮች ርቀው ትኩረታቸውን ንባብ ላይ እንዲያደርጉና የሚያነቡትን ለመረዳት እንዲሞክሩ ተማሪ ቢንያም መልእክቱን አስተላልፏል፡፡

በማበረታቻ ሽልማቱ 629 ነጥብ ያመጣው ተማሪ ቢንያም 6,000 ብር፣ 550 ያመጣው ተማሪ 5,000 ብርና ከ550-500 ያመጡ 4 ተማሪዎች እያንዳንዳቸው 4,000 ብር ተበርክቶላቸዋል፡፡ በት/ቤቱ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበ በመሆኑ የት/ቤቱ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህር ለነበሩትና በሞት ለተለዩት አቶ ወንዱ ዳባ ቤተሰብ 5,000 ብር በልዩ ሽልማት ድጋፍ ተደርጓል፡፡

በሽልማት መርሃ ግብሩ የት/ቤቱ ተማሪዎች፣ የተማሪ ወላጆች፣ መምህራንና ርዕሳነ መምህራን፣ የዩኒቨርሲቲውና የት/ቤቱ አመራሮች እንዲሁም የአርባ ምንጭ ከተማ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ ተገኝተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት