አርባ ምንጭ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከአራቱም ፋከልቲዎች ለተወጣጡ 19 መምህራን ‹‹Basic Python for Environmental Data Processing›› በሚል ርዕስ ከየካቲት 4-14/2015 ዓ/ም 2 ዙር የአሠልጣኞች ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የኢንስቲትዩቱ የአካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶ/ር ደመላሽ ወንድማገኘሁ እንደገለጹት ሥልጠናው ከዚህ ቀደም በተሰጠው የአሠልጣኞች ሥልጠና ላይ በተለያዩ ምክንያቶች ላልተገኙ መምህራን የተዘጋጀ ሲሆን በዩኒቨርሲቲው ለሚሠሩ ምርምሮች የሚሰበሰበውን መረጃ በአጭር ጊዜ ለማውረድና በቀላል መንገድ አገልግሎት ላይ እንዲውል በማድረግ ለመማር ማስተማርና ምርምር ሥራ እንዲጠቀሙ የሚያስችል ነው፡፡

በዩኒቨርሲቲው በቅድመና ድኅረ ምረቃ ትምህርት መርሃ ግብሮች ‹‹Basic Python Data Processing›› እንደአንድ ኮርስ በሥርዓተ ትምህርት ተካቶ መሰጠት መጀመሩን የጠቀሱት ዶ/ር ደመላሽ በዘርፉ የሠልጠኑ ባለሙያዎች ከተባባሪ ፕሮፌሰሮች ጋር በትብብር ኮርሱን እንዲሰጡ ለማስቻል እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው ለሌሎች ተቋማት የሥልጠና ጥያቄዎችን ለመመለስ ብቁ ባለሙያ እንዲያፈራ ይረዳል ብለዋል፡፡

በኔዘርላንድ ኢትሬክት ዩኒቨርቲ/Utrecht University/ የሚቲዎሮሎጂና ሃይድሮሎጂ ፋከልቲ መምህር የሆኑት አሠልጣኝ አቶ ኒምሮድ ዲ ዊት/Mr Nimrod de Wit/ ሥልጠናው የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎችን በተለይም ትላላልቅ መረጃዎችን በኮዲንግ በአጭር ጊዜ ለአገልግሎት እንዲውሉ አድርጎ ለምርምር ለመጠቀም የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኢንስቲትዩቱ የውኃ አቅርቦትና አካባቢ ምኅንድስና ፋከልቲ ዲን መ/ር ዘነበ ዓመለ ሥልጠናው በተለይ በውሃ አቅርቦትና አካባቢ ምኅንድስና ዘርፍ የሚሰበሰቡና ረዥም ጊዜ ሊፈጁ የሚችሉ የመረጃ አሰባሰብ ሥራዎች በአጭር ጊዜና ዘመኑ በደረሰበት ቴክኖሎጂ እንዲከናወኑ የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት