አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ 9ውን ሳይንስ ለዘላቂ ልማት ዐውደ ጥናት ከመጋቢት 01-02/2015 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ በዐውደ ጥናቱ 22 ዩኒቨርሲቲዎች የተሳተፉ ሲሆን በግብርና፣ ጤና እና የተፈጥሮ ሳይንስ መስኮች የተሠሩ 45 ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ዩኒቨርሲቲው ጥናትና ምርምሮችን በቁጥር፣ በዓይነትና በጥራት ለማሳደግ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ተናግረው የማኅበረሰቡን አኗኗር የሚያሻሽሉ ችግር ፈቺ ምርምሮችን በማካሄድና የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ብዙ ሥራ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡ ሳይንስና ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ የሀገሪቱን ዘላቂ ልማት ከማረጋገጥ አንጻር የምርምር ውጤቶችን፣ ሳይንሳዊ ሃሳቦችን፣ ልምድና ተሞክሮዎችን ለመጋራት መሰል መድረኮች ትልቅ ሚና እንዳላቸው ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡

የምርምር ዳይሬክቶሬት ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ካለበት አካባቢ አንጻር ምርምሮችን ለመሥራት ያሉትን መልካም አጋጣሚዎች ሲያቀርቡ ጋሞ ዞን ሁሉንም የአየር ንብረቶች የያዘና ለሙዝ፣ አፕል፣ እንሰት፣ ሞሪንጋ፣ ማሽላና የመሳሰሉ በዝቅተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ ቦታዎች የሚበቅሉ ሰብሎች ምቹ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ምርምሮችን የሚሠራበት መሬት ያለው መሆኑና የምርምር ማእከላትን፣ ቤተ ሙከራዎችንና ወርክሾፖችን ማደራጀቱ በተናጠልም ሆነ በጋራ ምርምር ለመሥራት ተመራጭ ያደርገዋልም ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጄኔቲክስ ኢመሪተስ ፕሮፌሰር እና የብዝሃ ሕይወት ጥበቃና ምርምር ኢንስቲትዩት ነባር አባል ፕሮፌሰር እንዳሻው በቀለ ‹‹ሳይንስ ለዘላቂ ልማት እና በኢትዮጵያ በተግባራዊነቱ ላይ ተጽዕኖ የሚያደርጉ ምክንያቶች›› በሚል ርእስ የዕለቱን ቁልፍ መልእክት ሲያስተላልፉ ልማትን ከሳይንስና ቴክኖሎጂ እድገትና ምጥቀት ውጪ ማሰብ እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ የሚያገኘውን ጥቅም ለማስጠበቅ ለምርምር ልማትና ፈጠራ ተገቢውን የሰው ኃይል፣ መሠረተ ልማትና ተቋማዊ አቅም መገንባትን ግብ ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት ፕሮፌሰር እንዳሻው ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለልማት እንዲውል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባሉበት አካባቢ የማኅበረሰቡን ችግር መሠረት አድርገውና መልካም አጋጣሚዎችን ተጠቅመው ምርምሮችን ሊሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡ ይህም ችግሩን በአግባቡ ለመረዳት፣ ድግግሞሽን ለማስቀረትና የምርምሮችን መሬት የመውረድ ዕድል ከፍ ለማድረግ እንደሚጠቅም ገልጸዋል፡፡

እንደ ፕሮፌሰር እንዳሻው የአፍሪካ ብሎም የኢትዮጵያ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ገጽታ ኋላ ቀር እንዲሆንና ለልማት እንዳይውል ካደረጉ ምክንያቶች መካከል የተመራማሪዎች ራስን ብቻ ማጉላትና ማስተዋወቅ፣ ያለፉ ችግሮችን መላልሶ በማውራት የመፍትሔ ሰው አለመሆን፣ ከሌሎች ሀገራት በቀጥታ መገልበጥና የቅንነት ማነስ ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡ ዘርፉን በማሳደግ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በቅንነትና በመናበብ መሥራት፣ ሳይንሳዊ ዲፕሎማሲን መረዳትና ለሀገር በቀል ዕውቀት በቂ ትኩረት መስጠት እንደሚገባቸው ፕሮፌሰር እንዳሻው ተናግረዋል፡፡

ሌላኛው የቁልፍ መልእክት አቅራቢ በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት እርባታ ተ/ፕሮፌሰርና የኢትዮጵያ እንስሳት እርባታ ባለሙያዎች ማኅበር አባል ዶ/ር ምትኩ እሸቱ ‹‹የአግሪቮልቴይክስ/Agrivoltaics/ ቴክኖሎጂ ለዘላቂ ልማት ያሉት ዕድሎች›› በሚል ርእስ ግብርናን ከፀሐይ ታዳሽ ኃይል ማምረት ጋር ማስተሳሰርን አስመልክቶ መልእክታቸውን አቅርበዋል፡፡

ዶ/ር ምትኩ በመልእክታቸው በማደግ ላይ ላለው የዓለም ሕዝብ በቂ ምግብ ማቅረብና ታዳሽ ኃይልን ማምረት የመጪው ዘመን ትኩረቶች መሆናቸውን ጠቅሰው ይህንን ለማሟላትና አሳሳቢ የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖዎች ለመቋቋም የአግሪቮልቴይክስ ቴክኖሎጂ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡ ቴክኖሎጂው የፀሐይ ታዳሽ ኃይልን ለመሰብሰብ በተዘረጉ መቀበያዎች/Solar Power Plants/ ሥር ዕፅዋትን በመትከል መሬቱን ለግብርናና ለፀሐይ ታዳሽ ሐይል ለመጠቀም የሚያስችል በመሆኑ ለተሻለ የመሬት አጠቃቀምና ዕፅዋቱን ከአላስፈላጊ የፀሐይ ጉዳት ለመጠበቅ ይጠቅማል፡፡ ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም ኢትዮጵያ ሰፊ አቅም ያላት ቢሆንም እስከ አሁን በሀገራችን ያልተሠራበት ነው ያሉት ዶ/ር ምትኩ ያደጉ ሀገራትን ተሞክሮ ወደ ሀገር ውስጥ አምጥቶ ለመጠቀም ዩኒቨርሲቲዎች ትኩረት ሰጥተው ምርምሮችን ሊያካሂዱ ይገባል ብለዋል፡፡

በዐውደ ጥናቱ ከቀረቡ ምርምሮች መካከል አንዱ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲው ዶ/ር መንዴ መንሳ ‹‹The Current Challenges of the Ethiopian Health Insurance System from Financial Protection, Equitable Access to Medicines and Financial Viability of Insurance Organization Perspective›› በሚል ርእስ ያቀረቡት ሲሆን በጥናታቸው በኢትዮጵያ የጤና መድኅን ሥርዓት ከፋይናንሺያል ጥበቃ፣ ከመድኃኒት ፍትሃዊ ተደራሽነት እና ከመድኅን ድርጅት የፋይናንስ አዋጭነት አንጻር ያሉ ተግዳሮቶችን ዳስሰዋል፡፡ የጤና መድኅን ሥርዓቱ መፍትሔ ካልተበጀለት ድርጅታዊ ኪሳራ በሚያስከትል መልኩ ችግሮች የተጋረጡበት በመሆኑ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት በማካተት ችግሮቹን መፍታትና የሥርዓቱን ቀጣይነት ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡

ሌላኛው ጥናት አቅራቢ ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ዶ/ር ዘነበ ይርጉ በቅርብ ጊዜያት በቆሻሻ ውኃ ማጥራትና በባዮፊውል ማምረት ላይ ተስፋ ሰጪ ግብዓት በሆነው ማይክሮአልጌ/Microalgae/ ላይ ያደረጉትን ጥናት ‹‹Potential of Local Microalgae for Coupling Agro-industrial Wastewater Remediation with Lipid and Bioethanol Production›› በሚል ርእስ አቅርበዋል፡፡ ጥናቱ የግብርናና ኢንደስትሪ ፍሳሾችን በማጥራትና በባዮኢታኖል/ Bioethanol ማምረት ሂደት የማይክሮአልጌን አቅም ለመለካት የተሠራ መሆኑን ዶ/ር ዘነበ ገልጸዋል፡፡ እንደ ተመራማሪው ማይክሮአልጌ በአካባቢያችን በብዛት የምናገኘውና የሚጠቅም የማይመስለን ቢሆንም በዓለማችን በርካታ ጥናቶች እየተሠሩበት ያለና በመዋቢያ ምርቶች፣ መድኃኒቶች፣ ቆሻሻ ውኃን ማጣራት፣ ባዮፊውልና ማዳበሪያ ኢንደስትሪዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚሰጥ ነው፡፡ በጥናታቸው እንዳመለከቱት ከቢራ ፋብሪካ በተወሰደ ውኃ ላይ አረንጓዴ ማይክሮአልጌን በማሳደግ በላቦራቶሪ ደረጃ የውኃ ማጥራት ደረጃውን ማየትና ባዮኢታኖል ማምረት ተችሏል፡፡ ጥናቱ በላቦራቶሪ ደረጃ የተሠራ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ዘነበ በቀጣይ በፓይለትና በሙሉ ጥናት ደረጃ ቢሠራ ለተለያዩ ኢንደስትሪዎች ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማእከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት