በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ-ሰብ ኮሌጅ የእንግሊዝኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ ት/ክፍል በሥራ ላይ ያሉ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህራንን ሙያዊ ብቃት ማሻሻል ‹‹Improving English Language Teachers’ Professional Competency through Need-Based on-Job Training››  በሚል ርዕስ የግራንድ ምርምር ማስጀመሪያ መርሃ ግብር መጋቢት 2/2015 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምር ዳይሬክቶሬት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተርና የምርምርና ማኅ/ጉድ/ም/ፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ተስፋዬ ሀብተማርያም የመምህራን የሙያ ብቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወረደ መምጣቱ የሙያውን ክብር እየቀነሰው መሆኑን ገልጸው ሙያውን እንደተከበረ ለማቆየት የመምህሩ ፍላጎት፣ ተነሳሽነትና ራስን ለማሻሻል ያለው ቁርጠኝነት አስተዋጽዖ አለው ብለዋል፡፡ በመሆኑም የፌዴራል፣ የዞንና የወረዳ መንግሥት ሁሉም የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባና የመምህራን ማሠልጠኛ ተቋማት እና መምህራንም ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው ዶ/ር ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡  

አክለውም ፕሮጀክቱ ይዞ የተነሳውን የመምህራን የሙያ ብቃት የማሻሻል ዓላማ እውን በማድረግ የመጪው ትውልድ የወደፊት እጣ ፈንታ የሰመረ እንዲሆን እንዲሁም ሀገሪቱም የተሻለ መሪና ሀገር ተረካቢ እንዲኖራት በቋንቋው ላይ በትኩረት በመሥራት የትምህርት ጥራት ሊመጣ ይገባል ብለዋል፡፡ ባለድርሻ አካላትም ከዩኒቨርሲቲው ጋር በጋራ ሊሠሩ እንደሚገባና የፕሮጀክቱ ሂደት በታቀደው ልክ መተግበሩን መከታተል፣ ድጋፍና እገዛ ማድረግ፣ ፕሮጀክቱ ሲያበቃ መምህራንን የማብቃት ጥረቱን ማስቀጠልና ውጤታማ እንዲሆን ማድረግ እንደሚገባ ዶ/ር ተስፋዬ አሳስበዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የእንግሊዝኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ ት/ክፍል መምህርና የፕሮጀክቱ ዋና ተመራማሪ ዶ/ር እንደልቡ ጎኣ በበኩላቸው የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ ለእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህራን የተለያዩ የሥራ ላይ ሥልጠናዎችን በመስጠትና ሙያቸውን እንዲያሻሽሉ በማድረግ የሚያስተምሩትን ትምህርት የማሳወቅ ብቃታቸውን እንዲሁም የማስተማሪያ ሥነ ዘዴያቸውን ማሻሻል መሆኑን ገልጸዋል፡፡  በፕሮጀክቱ የቆይታ ጊዜም በጋሞ ዞን ካምባ፣ ገረሴ፣ ጨንቻ፣ ምዕራብ ዓባያና ቦረዳ ወረዳዎች እንዲሁም በአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ ሁለት ት/ቤቶች ላይ በሚካሄደው የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት የተገኙ ውጤቶችን መነሻ በማድረግ የሥልጠና ግብዓቶች ተዘጋጅተው ሥልጠናዎችን በመስጠት የሚመጣው ለውጥ እየተገመገመ ተከታታይ ሥልጠናዎች የሚሰጡ መሆኑን ዋና ተመራማሪው ገልጸዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ለ3 ዓመታት የሚቆይና ለሥራው ማስፈጸሚያ በዩኒቨርሲቲው 1,750,000.00/አንድ ሚሊየን ሰባት መቶ ሃምሳ ሺህ/ ብር የተመደበለት ሲሆን ተከታታይ የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና /CPD/ን ትኩረት በማድረግ በቀጣይ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህራንን ፍላጎት መሠረት በማድረግ የትምህርት ዘርፉን ይበልጥ በሚያጠናክር መልኩ ተግባራዊ እንደሚደረግ ዶ/ር እንደልቡ ተናግረዋል፡፡

የማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ-ሰብ ኮሌጅ የምርምር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር እንዳልካቸው ኃይሉ የመምህራን የቋንቋ ችሎታና የማስተማር ሥነ-ዘዴ ብቃታቸው ያለበትን ደረጃ በመገምገምና በመፈተሽ ውጤቱን መሠረት ያደረጉ የተለያዩ የሥልጠና ግብዓቶች እንደሚዘጋጁ እና ለትምህርት ሴክተር መ/ቤቶች እንዲሁም ለመምህራን እንዲደርሱ እንደሚደረግ፣ የትምህርት መምሪያውም ፕሮጀክቱ ጊዜውን ሲጨርስ ኃላፊነቱን ተቀብሎ እንደሚያስቀጥልና በሂደት የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህራን የቋንቋ ብቃት በዘላቂነት እየተሻሻለ የሚሄድበት ሥርዓት እንደሚዘረጋ ተናግረዋል፡፡

መሰል ፕሮጀክቶችን በማምጣት ረገድ የተጠናቀቁና በመጠናቀቅ ላይ ያሉ 5 ፕሮጀክቶች መኖራቸውን የጠቆሙት ዶ/ር እንዳልካቸው አብዛኞቹ የቋንቋ ክሂሎትን በማሻሻል ላይ ትኩረት ያደረጉ ናቸው ብለዋል፡፡ ግራንድ ፕሮጀክቶቹ ወደ መሬት ወርደው የመምህራንን የሙያ ብቃትና የትምህርት ጥራት እንዲሻሻል የበኩላቸውን አስተዋፅዖ የሚያበረክቱ በመሆናቸው በቀጣይ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ቢመጡ እንደሚበረታቱም አክለዋል፡፡

የሥነ-ትምህርትና ሥነ-ባህርይ ሳይንስ ት/ቤት መምህር እና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ረ/ፕሮፌሰር ሰለሞን ሳጶ እንግሊዝኛ ቋንቋ ለመማር ማስተማር ሂደት ቁልፍ በመሆኑ መምህራን ቋንቋውን በተገቢው መንገድ ሊያውቁና ሃሳባቸውን ሊገልጹበት እንደሚገባ እንዲሁም የሚስተዋለውን የማስተማር ክሂሎት ክፍተት በመቅረፍ የሚያውቁትን በአግባቡ ለተማሪዎች በማሳወቅ በዕውቀትና በቋንቋ ክሂሎት የተሻለ ትውልድን ለማፍራት መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡ በፕሮጀክቱ ቆይታም ባለድርሻ አካላት ሂደቱን እንዲከታተሉና የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በማቅረብ ረገድ ከጎናቸው ይሆኑ ዘንድ ጠይቀዋል፡፡   

የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ረገድ በትኩረት በመሥራት ትውልዱን ከውድቀት ልናድነው ይገባል ያሉት የጋሞ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አብርሃም አምሳሉ ፕሮጀክቱ በአካባቢው የትምህርት ዘርፍ ላይ ያለውን ችግር ለይቶ ለመቅረፍ የታቀደበት እንደመሆኑ ብቃት ያላቸው ተማሪዎችን ለማፍራት ብሎም ከፍተኛ የተማረ የሰው ኃይል እጥረት እንዳይገጥምና የሥራ አጥ ቁጥር እንዳይጨምር መምህራን በፕሮጀክቱ በመታቀፍ የግል ብቃታቸውን ማሻሻል እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም እንደ ዞን በተማሪዎችና መምህራን ሥነ-ምግባር፣ በት/ቤቶች የትምህርት አመራር ክሂሎት፣ በሳይንስ ትምህርቶች እና ለ1 ደረጃ ተማሪዎች በንባብና ጽሕፈት ክሂሎት ላይ ዩኒቨርሲቲው ፕሮጀክት ቀርጾ እንዲሠራና እንደ ባለድርሻ አካል ድጋፍ እንዲያደርግ አቶ አብርሃም ጠይቀዋል፡፡

በዕውቀትና በማስተማር ክሂሎት ረገድ በመምህራን ላይ ብዙ መሥራት ያስፈልጋል ያሉት የፕሮግራሙ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ፕሮጀክቱ ይዞት የተነሳው ዓላማ የቋንቋ መምህራንን በቋንቋ ማብቃትና ተማሪዎች ተገቢውን ትምህርት እንዲያገኙና ውጤታማ እንዲሆኑ ማድረግ በመሆኑ የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ውስንነት እንዳይታይበትና በዘላቂነት ሁሉም መምህራን ተጠቃሚ እንዲሆኑ መሥራት ያሻልም ብለዋል፡፡   

በፕሮግራሙ ከጋሞ ዞን ካምባ፣ ገረሴ፣ ቦረዳ፣ ጨንቻና ምዕራብ ዓባያ ዙሪያ ወረዳዎች እና ከአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር የተወጣጡ የትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ መምህራን፣ ር/መምህራን እና የጋሞ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው የምርምር ዳይሬክቶሬት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተርና የምር/ማኅ/ጉድ/ም/ፕ/ተወካይ፣ የማኅበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ ም/ዲን፣ የእንግሊዝኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ ት/ክፍል መምህራንና ተመራማሪዎች እንዲሁም የሥነ-ትምህርት ሳይንስ ት/ክፍል አስተባባሪዎች ተገኝተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት