የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና ማዕከል ማስ/ጽ/ቤት ከአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ጤና ጽ/ቤት ጋር በመተባበር በከተማው ከሚገኙ ሆስፒታልና ጤና ጣቢያዎች ለተወጣጡ የጤና ባለሙያዎች በወባ በሽታ ምርመራ፣  ሕክምና አሰጣጥ፣ ቁጥጥርና መከላከል አዳዲስ አሠራሮች ዙሪያ ከመጋቢት 1-3/2015 ዓ/ም ድረስ የቆየ የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የኮሌጁ የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና ማዕከል ማስ/ጽ/ቤት ኃላፊ ተባባሪ ፕሮፌሰር ፈለቀ ገ/መስቀል ኮሌጁ በተለያዩ ጤና ተቋማት ለሚያገለግሉ ለሕክምናና ጤና  ባለሙያዎች የረጅምና የአጭር ጊዜ የሥራ ላይ ሥልጠናዎችን በመስጠት አቅማቸውን የማጎልበትና ከዘርፉ አዳዲስ አሠራሮችና ግኝቶች ጋር የማስተዋወቅ ሥራን በትኩረት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሥልጠናው በዋናነት በወባ በሽታ ምርመራ፣ ሕክምና አሰጣጥ፣ ቁጥጥርና መከላከል አዳዲስ አሠራሮች ዙሪያ በማተኮር ከድል ፋና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል እና ከሴቻና ወዜ ጤና ጣቢያዎች ለተወጣጡ 35 የጤና ባለሙያዎች የተሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡  የበሽታውን ሕክምና አሰጣጥ፣ ምርመራና የመከላከል ሥራን ማሻሻል የሥልጠናው ዋነኛ ግብ መሆኑን የገለጹት አስተባባሪው በወባ በሽታ ሕክምና አሰጣጥንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የተዘጋጀውን አዲስ ፕሮቶክልን ለባለሙያዎቹ ማስገንዘብ ሌላኛው የሥልጠናው ትኩረት መሆኑን አውስተዋል፡፡

ማዕከሉ ሥልጠና ከማዘጋጀትና ከመስጠት ባሻገር ለጤና ባለሙያዎች ለሙያ ዕድሳት ማገልገል የሚችል የምስክር ወረቀት የመስጠት ኃላፊነት በጤና ሚኒስቴር የተሰጠው መሆኑን የገለጹት ተ/ፕሮፌሰሩ ለሠልጣኞቹ ከሥልጠናው መጠናቀቅ በኋላ የሚሰጠው የምስክር ወረቀትም ከዚህ አንፃር የሚጠቅም ነው ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሳዴማ ሻንቆ በበኩላቸው አርባ ምንጭና አካባቢው በጋሞ ዞን ውስጥ ከሚገኙ አካባቢዎች ከደራማሎ ወረዳ በመቀጠል ክፍተኛ የወባ ስርጭት ያለበት አካባቢ መሆኑን ገልጸው የከተማ አስተዳደሩ በሽታውን ለመከላከል ብሎም ለመቆጣጠር የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በከተማችን ለሚገኙ የጤና ባለሙያዎች የተሰጠው ሥልጠና የባለሙያዎችን ዕውቀት ከማዳበር፣ ወቅታዊ ከማድረግ፣ ለማኅበረሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት ከማሻሻል ባለፈ በሽታውን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና ለማከም የሚደረጉ ጥረቶችን በእጅጉ የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡ መሰል የሙያ ማሻሻያ ሥልጠናዎችን ማግኘት መቻል ለጤና ባለሙያዎች ትልቅ ዕድል መሆኑን የገለጹት አቶ ሳዴማ ባለሙያዎቹ የተሻለና ወቅታዊ ዕውቀት ከማግኘታቸው ባሻገር የሚሰጣቸው የምስክር ወረቀት ለሙያ ፍቃድ ዕድሳት ይጠቅማቸዋልም ብለዋል፡፡

ከአሠልጣኞች መካከል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ሐኪምና የኮሌጁ መ/ር ዶ/ር ታዲዮስ ኃይሉ የወባ በሽታ ፕላስሞዲየም በተሰኘ ጥገኛ ተህዋስ አማካኝነት የሚከሰትና በወባ ትንኝ ንክሻ ምክንያት ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍና ከዓለማችን ዋነኛ ገዳይ በሽታዎች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የወባ በሽታ በአንዳንድ አካባቢዎች ከመቀነስ ይልቅ የመጨመር አዝማሚያ እያሳየ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ታዲዮስ ለዚህም በሕክምና ሥራው ላይ በቀጥታ የሚሳተፉ ባለሙያዎችን አቅም ማጎልበትና ከአዳዲስ አሠራሮችና ግኝቶች ጋር ማስተዋወቅ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡ ከወባ በሽታ ምርመራ፣ መድኃኒት አሰጣጥና አወሳሰድ ዙሪያ ምርምርን መሠረት አድርገው የተቀየሩ አዳዲስ አሠራሮች መኖራቸውን የገለጹት አሠልጣኙ ሥልጠናው ከአዳዲስ ግኝቶችና አሠራሮች ጋር ባለሙያዎቹን በማስተዋወቅ በሽታው የሚያስከትላቸውን ጉዳቶች ከመቀነስ አንፃር ብሎም እንደ ሀገር በሽታውን ለማጥፋት የተያዙ ሀገራዊ ዕቅዶችን ተግባራዊ ለማድረግ ጉልህ ሚና ይጫወታልም ብለዋል፡፡

ከሠልጣኞች መካከል በሴቻ ጤና ጣቢያ የጤና መኮንና በተመላላሽ ሕክምና ክፍል ሠራተኛ አቶ ሙሉጌታ ነጋሽ የወባ ሕሙማን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን ገልጸው በሥልጠናው ከወባ በሽታ ሕክምና ጋር ከተያያዙ የተለያዩ አዳዲስና የተከለሱ አሠራሮች ጋር የተዋወቁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ሳይንስ ተለዋዋጭ መሆኑን ያወሱት አቶ ሙሉጌታ መሰል ሥልጠናዎች ከአዳዲስ የሳይንስ ግኝቶች ጋር ባለሙያው እንዲተዋወቅ፣ የተረሱ ጽንሰ ሃሳቦችን እንዲያስታውስ፣ የተቀየሩ የመድኃኒት አሰጣጦችን ከመገንዘብ  አንፃር የጎላ ሚና ይኖረዋልም ብለዋል፡፡ በሥልጠናው የተገኙት አዳዲስ ዕውቀቶች የሚሰጠውን የወባ በሽታ ሕክምና አሰጣጥና አስተዳደር የሚያሻሽሉና ለማኅበረሰቡ በመስኩ የሚሰጡ አገልግሎቶችን አንድ ደረጃ ከፍ የሚያደርግ እንደሆነም አቶ ሙሉጌታ አክለዋል፡፡

በሥልጠናው ማጠቃለያ ላይ ለሠልጣኞች የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት