የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ለአዲስ ገቢ ሴት ተማሪዎች ከመጋቢት 01-02/2015 ዓ/ም የሕይወት ክሂሎት/Life Skill/ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

 የዳይሬክቶሬቱ ዳይሬክተር ወ/ሪት ሠናይት ሳህሌ እንደገለጹት ሥልጠናው ሴት ተማሪዎች በመማር ማስተማር፣ በአስተዳደር እንዲሁም በካምፓስና በግል ሕይወታቸው የሚገጥሟቸውን ተፈጥሯዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖዎች አሸንፈው እንዲወጡ የሚረዳቸው ነው፡፡ ሴት ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ሊገጥሟቸው የሚችሉ ተግዳሮቶችን ቀድመው ዐውቀው የጊዜ አጠቃቀምና የአጠናን ዘዴያቸውን እንዲያስተካክሉ፣ በራስ የመተማመን ስሜታቸውን እንዲያጎለብቱ፣ በፈተና ጊዜ ከሚያጋጥም ጭንቀት ራሳቸውን እንዲከላከሉ ብሎም ከ‹‹HIV/ADIS››ና ከሥነ ተዋልዶ ጤና ችግሮች ተጠብቀው በትምህርታቸው ብቁና ለሀገር የሚጠቅሙ ዜጋ እንዲሆኑ በማለም የተዘጋጀ ሥልጠና መሆኑን ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና አሠልጣኝ ዮሴፍ ዓለማየሁ ሥልጠናው በፈተና ጊዜ የሚመጣ ጭንቀት፣ ያልተፈለገ እርግዝና፣ ጾታዊ ትንኮሳ፣ የጊዜ አጠቃቀም፣ የአቻ ግፊትና የመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ በማስጨበጥ ሴት ተማሪዎች ዓላማቸውን እንዲያሳኩ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሠልጣኝ ተማሪዎች ከሥልጠናው ለትምህርታቸውም ሆነ ለማኅበራዊ ሕይወታቸው የሚጠቅሙ በርካታ ክሂሎቶችን ማግኘታቸውን ተናግረው ባገኙት ዕውቀት ብቁ ተወዳዳሪ በመሆን ራሳቸውንና ሀገርን ለመጥቀም በትጋት እንደሚማሩ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማእከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት