የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ት/ቤት ከጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጋር በመተባበር በገጠር መሬት አዋጅና ይርጋ ዙሪያ በጋሞ ዞን፣ በዞኑ ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች ለሚገኙ የፍርድ ቤት ፕሬዝደንቶችና ዳኞች መጋቢት 09/2015 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ፎቶ ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ሕግ ትምህርት ቤት ዲን መ/ር እንየው ደረሰ እንደገለጹት የሥልጠናው ዓላማ በጋሞ ዞን ያሉ ፍርድ ቤቶች በገጠር መሬትና የገጠር መሬት አዋጅን መሠረት ያደረጉ ውሳኔዎችና የመብት ጥያቄዎችን አስመልክቶ ግንዛቤ በማስጨበጥ በውሳኔ አሰጣጥ ረገድ ያለውን ልዩነት ማጥበብ እና በዞኑ አንድ ወጥ የሆነ አሠራርና ምልከታ እንዲኖርና ትክክለኛ የፍትሕ ሥርዓት እንዲሰፍን ማስቻል ነው፡፡ የሕግ ት/ቤት ከመማር ማስተማር ጎን ለጎን በጋሞ፣ ጎፋና ኮንሶ ዞኖች ውስጥ ባሉ የተለያዩ ወረዳዎች አቅም ለሌላቸው ሴቶች፣ አረጋውያን፣ ሕፃናት እና አካል ጉዳተኞች ፍርድ ቤት ወክሎ በመከራከር በነፃ ጥብቅና፣ ማስረጃዎችን በመጻፍ፣ በሕግ ምክር አገልግሎት እና ሥልጠናዎችን በመስጠት ፍትሕ እንዲያገኙ እያደረገ መሆኑን ዲኑ ተናግረዋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ እንደ ፖሊሲ በተያዘውና የህልውና ጉዳይ በሆነው የመሬት ጉዳይ ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ሲሰጡ በተጨባጭ ያለውን ፖሊሲ ከግንዛቤ በማስገባት እንዲሠሩ ከማጠናከር አኳያ ት/ቤቱ በትኩረት እየሠራ መሆኑንም አቶ እንየው ጠቁመዋል፡፡  

የተፈጥሮ መብት የሆነውን የፍትሕ ጥያቄ የመመለስ ኃላፊነታችንን ያለ አንዳች ማዳላት ተግባራዊ ልናደርግ ይገባል ያሉት የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት አቶ ጩባሮ ጮንደሮ ሥልጠናው የፍርድ ቤት ዳኞች ከገጠር መሬት አዋጅ ጋር ተያይዞ ያለውን የውሳኔ ጥራት በመጠበቅ ሕግን መሠረት አድርገው በአግባቡ እንዲሠሩ እና በዕውቀት የተመራ የዳኝነት አሰጣጥ ሥርዓት እንዲኖር ታቅዶ የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡ መድረኩ ዳኞች ልምድና ዕውቀታቸውን የሚለዋወጡበት ብሎም በሕግ ጉዳዮች ላይ አንድ ወጥ የሆነ የጋራ ግንዛቤ የሚይዙበት መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዝደንቱ በቀጣይም በሕግ ት/ቤቱ ዕቅድ መሠረት በቅንጅት እስከ ወረዳ ፍርድ ቤቶች ተደራሽ የሚሆኑ ሥራዎችን እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ሕጎችን አስመልክቶ ሥልጠና የሰጡት የዩኒቨርሲቲው የሕግ አገልግሎት    ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እና የሕግ ትምህርት ቤት መምህር አቶ ዳኛቸው ወርቁ እንደገለጹት የገጠር መሬት ላይ ትልቁ መብት የይዞታ መብት ሲሆን በተለይ አርብቶ አደሮችና አርሶ አደሮች የገጠር መሬት ላይ የይዞታ መብት እንዳላቸውና ሕጉም ከሌሎች ጠቅላላ ሕጎች ጋር አብሮ መታየት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም የገጠር መሬት ላይ ያሉ በተለይም የንብረት፣ ውርስ እና ውል መብቶችን በሚመለከት የፌዴራልም ሆነ የክልል ሕገ መንግሥቶችን በደንብ ማየት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

እንደ መ/ር ዳኛቸው አንድ የገጠር መሬት ባለይዞታ በግብርናና በተፈጥሮ ሀብት ልማት መሬቱን የመጠቀም፣ ለቤተሰብ አባል በስጦታና በውርስ የማስተላለፍ፣ መሬቱን ተከትለው የሚመጡ ማንኛውንም ዓይነት የሀብት ምንጮች የመሸጥና የመለወጥ መብቶች ያሉት ሲሆን የገጠር መሬት ይዞታው የሚገኘው በድልድል ወይም በሽግሽግ፣ በውርስና ስጦታ እንጂ በሽያጭና በመያዣ ከሆነ የገጠር መሬት ባለይዞታ መሆን እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡

በደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክ መንግሥት የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ 110/99 እና በይርጋ ሕጎች ላይ ያተኮረ ሰነድ ያቀረቡት የጋሞ ዞን ም/ፕሬዝደንት እና ዳኛ አቶ አንዷለም አምባዬ ይርጋ የአንድ ሰው የመብት ጥያቄ በጊዜ ማለፍ ምክንያት ቀሪ የሚሆንበትን በአንጻሩ ሌላኛው ወገን የመብት ባለቤት የሚሆንበትን የሕግ መርህ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

እንደ አቶ አንዷለም የይርጋ ጥቅም ሐሰተኛ ክስና ማስረጃን መከላከል፣ ተከራካሪ ወገኖችን ማንቃት፣ የይዞታ ሰላምን መጠበቅና ቸልተኛ ባለንብረቶችን መቅጣት ሲሆን ይርጋ እንደ መጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ሆኖ ሲቀርብ ጉዳዩን በብይን ሊያስቆም የሚችል በመሆኑ የይርጋ መቃወሚያው ነጥብ በአግባቡና በጥልቀት ሊመረመር ይገባል፡፡ የይርጋ ጥያቄው በመሃል የተቋረጠበት ሁነት መኖር አለመኖሩ፣ ጊዜው መቆጠር ያለበት ከመቼ ጀምሮ እንደሆነ፣ በገጠር መሬት ክርክር ላይ ሲሆን ይዞታውን አብረው ግራ ቀኝ ያስተዳደሩ መሆን አለመሆኑ በሚገባ ሊታይ እንደሚገባና በዚህ ሂደት እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችን አሠልጣኙ በዝርዝር አንስተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ፍትሕ ለአንድ ሀገር እድገትና ሁለንተናዊ ለውጥ ቁልፍ ሚና ያለው በመሆኑ ኅብረተሰቡ የደረሰበትንና ወደ ፊት ሊደርስበት የሚፈልገው የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማኅበራዊ ኑሮ እድገት ደረጃን ያንጸባርቃል ብለዋል፡፡ ስለሆነም የፍትሕ ይዘት ጥራትና ዓይነት፣ የፍትሕ አደረጃጀት፣ አወቃቀርና አመቺነት፣ የፍትሕ መተግበሪያ ዘዴና ስትራቴጂ እንዲሁም አጠቃላይ ሥርዓተ ፍትሕ ግልጽ ሊሆንና በተገቢው መንገድ ሊመራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው የሕግ ጉዳዮችን በጥልቀት በመመርመርና በመረዳት በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ  ሕገ መንግሥቱን መሠረት ያደረጉ ትክክለኛ ውሳኔዎችን እንድንወስን አቅጣጫ የሚያስይዝ ነው ብለዋል፡፡ የሕግ ትምህርት ቤቱ ሥልጠናዎችንና የምክክር መድረኮችን በማዘጋጀት ማኅበረሰቡ ፍትሕ እንዲያገኝ ለሚያደርገው ጥረትም አመስግነዋል፡፡ 

በሥልጠናው ርዕሰ ጉዳዮችና በአሠራር ሂደት በተደጋጋሚ በሚያጋጥሙ ችግሮች ዙሪያ የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተው ሰፊ ውይይት የተካሄደ ሲሆን የመፍትሔ አቅጣጫዎችም ተቀምጠዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት