የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እንስሳትና ዓሳ ሀብት ምርምር ማእከል ሳሶ ብሮይለር ብሪድ/Saso Broiler Breed/ ዝርያ ያላቸው ሁለት ሺህ ጫጩቶችን በግዥ በማስመጣት ያስጀመረው የዶሮ እርባታ ጣቢያ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች እና የማእከሉ ተመራማሪዎች በተገኙበት መጋቢት 7/2015 ዓ/ም ተጎብኝቷል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የማእከሉ ዳይሬክተር አቶ እሳቱ በቀለ ማእከሉ ካቀዳቸው ዘርፈ ብዙ ሥራዎች መካከል የድለባ ዶሮዎችን ለማኅበረሰቡ ማቅረብ አንዱ መሆኑን ገልጸው በቅርቡ የተሻሻሉ የእንቁላል ዶሮዎችን በማስመጣት ምርቱን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማኅበረሰቡ ለማቅረብ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ ማእከሉ ለጊዜው የሳሶ ብሮይለር ብሪድ ዝርያና ለሥጋ የሚሆኑ ሁለት ሺህ የድለባ ጫጩቶችን በማስመጣት ሥራ መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡

በማእከሉ የእንስሳት ጤና ተመራማሪ ዶ/ር መስፍን ሹሩቤ ከሁለት ወራት በኋላ ለማኅበረሰቡ በሽያጭ የሚቀርቡ የ45 ቀን ዕድሜ ያላቸውን ጫጩቶች በመረከብ ሥራ መጀመራቸውን በመግለጽ በቀጣይም ለዩኒቨርሲቲውና ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሚያገለግል የዶሮ ጫጩት ማስፈልፈያ የማቋቋም፣ የዶሮ መኖና እንቁላል ምርቶችን በሽያጭ የማቅረብና ሌሎች ሰፊ ሥራዎችን ለመሥራት መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅ/ጉድ/ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ ዩኒቨርሲቲው በዓሳ ሀብት፣ በከብት እርባታና በወተት ተዋፅዖ፣ በንብ ማነብና በማር እንዲሁም በዶሮ እርባታ በተቀናጀ ሁኔታ ለአካባቢው ማኅበረሰብ አገልግሎት በመስጠትና ምርምር በማካሄድ እንደ ሀገር የተጀመረው ‹‹የሌማት ትሩፋት›› ፕሮግራም እንዲሳካ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል፡፡

ም/ፕሬዝደንቱ አክለው እንደገለጹት በቀጣይ የእንስሳት እርባታን በማዘመን የተሻሻሉ ዝርያዎችን አባዝቶና ለይቶ ለማኅበረሰቡ ለማስተላለፍ እየተሠራ ነው፡፡ ለሥጋ የሚሆኑ የዶሮ ዝርያዎችን የመለየቱ ሥራ በዩኒቨርሲቲው በዘርፉ ልምድ ባላቸው ባለሙዎያች፣ የዶሮ ሥርዓተ ምግብ ምሁራንና በማእከሉ ተመራማሪዎች መመራቱን የጠቆሙት ም/ፕሬዝደንቱ ዶሮዎቹን በአጭር ጊዜ ውስጥ በማድረስ ማኅበረሰቡ እንዲጠቀም ይደረጋል ብለዋል፡፡

በጉብኝቱ ወቅት የዩኒቨርሲቲው አመራሮች የተሠሩ ሥራዎችን ምልከታ በማድረግ ለማእከሉና ለተመራማሪዎቹ የተለያዩ አስተያየቶችን የሰጡ ሲሆን በቀጣይ ለሚሠሯዋቸው ሥራዎችም ዩኒቨርሲቲው ድጋፍ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡

                                                                                         አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

                                                                                          የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
                                                                                      የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት