የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ለጫሞ ካምፓስ አዲስ ገቢ ሴት ተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበልና የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ የ3እና 4 ዓመት ሴት ተማሪዎች የማበረታቻ መርሃ ግብር መጋቢት 7/2015 ዓ.ም አካሂዷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲንና የጫሞ ካምፓስ ኃላፊ ዶ/ር መስፍን መንዛ መርሃ ግብሩ ለሴቶች በልዩነት መዘጋጀቱ ሴት ተማሪዎች በተቋሙ የሚሰጡ አገልግሎቶችን የተመለከቱ መረጃዎችን በተገቢው ሁኔታ እንዲያገኙና በቀለም ትምህርት ብቻ ሳይሆን በሥነ-ምግባርም መታነጽ እንዲችሉ ያግዛል ብለዋል፡፡ ለውጤታማ ሴት ተማሪዎች የተሰጠው ማበረታቻ ሽልማትም የተሻለ ውጤት ያመጡትን ሴት ተማሪዎች የሚያበረታታና ሌሎች አዲስ ገቢዎችን የሚያነሳሳ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር መስፍን ተማሪዎቹ በሚኖራቸው የትምህርት ቆይታም ውጤታማ ለማሆን ጠንክረው እንዲሠሩ አሳስበዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ቡድን መሪ አቶ ዛፉ ዘውዴ  በበኩላቸው ሴት ተማሪዎች በትምህርት ቆይታቸው በተለያዩ አካላት ጾታዊ ትንኮሳና ጥቃት ሊደርስባቸው እንደሚችል በመረዳት አስፈላጊውን ጥንቃቄና የሥነ-ልቦና ዝግጅት ማድረግ፣ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩ ጓደኞች መራቅ፣ ትምህርታቸው ላይ ማተኮር፣ ጊዜያቸውን በአግባቡ መጠቀምና ወሲባዊ ትንኮሳዎች ሲደርሱባቸው በዳይሬክቶሬቱ አማካኝነት አስፈላጊ የሕግ እርምጃ  እንዲወሰድ ማድረግ እንደሚገባቸው አመላክተዋል፡፡

ለውጥ ለማምጣት የራስ ፍላጎትና የውስጥ ተነሳሽነት እንደሚያስፍልግ የገለጹት በጫሞ ካምፓስ የሴት መምህራን ኔትዎርክ ም/ሰብሳቢና የሶሲዮሎጂና ሶሻል አንትሮፖሎጂ ትምህርት ክፍል መ/ርት ባንቺይደሩ አወል በተቋሙ ለሴት ተማሪዎች በርካታ  ምቹ ሁኔታዎች እንዳሉም ጠቁመዋል፡፡ ም/ሰብሳቢዋ ሴት ተማሪዎች የመጡበትን ዓላማ ሳይዘነጉ በተገቢው ሁኔታ ትምህርታቸውን መከታተል ከቻሉና በራስ መተማመን መንፈሳቸውን ማጎልበት ከቻሉ ስኬታማ መሆን እንደሚችሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በመርሃ-ግብሩ ከፍተኛ ውጤት ያመጡና ተሸላሚ ሴት ተማሪዎች የተማሪነት ልምዳቸውን ያቀረቡ ሲሆን የዜሮ ፕላን ማዕከል ተጠቃሚ ተማሪዎችም ስለማዕከሉ ተግባራት ገለጻ አቅርበዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት