አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በጋሞ ዞን ካምባ ዙሪያ ወረዳ በዝናብ እጥረት ምክንያት ለድርቅ ለተጋለጡና አስቸኳይ የምግብ እህል ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች 70 ኩንታል የምግብ በቆሎ መጋቢት 18/2015 ዓ/ም በካምባ ከተማ ተገኝቶ አስረክቧል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገዝሙ ቃልቦ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ቀደም ሲል ዛላ፣ ደራሼ፣ ኮንሶና ቦረና አካባቢዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በቆሎ፣ ሩዝና የመሳሰሉ የምግብ እህሎችን በየአካባቢው ተገኝቶ ድጋፍ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን በካምባ ወረዳም በገንዘብ ሲተመን ከ230 ሺህ ብር በላይ የሚያወጣ በቆሎ ድጋፍ አድርጓል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ሥራው ጎን ለጎን ለማኅበረሰቡ ችግር ለመድረስና አጋርነቱን ለማሳየት እንደሚሠራ የተናገሩት የጽ/ቤት ኃላፊው የተደረጉት ድጋፎች ሌሎች አካላት ድጋፍ ከሚፈልጉ ወገኖች ጎን እንዲቆሙ አርአያ ለመሆንም ጭምር ነው ብለዋል፡፡

የካምባ ዙሪያ ወረዳ ም/አስተዳዳሪና የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መሳፍንት ኃ/ሚካኤል በዙሪያ ወረዳው ካሉ 32 ገጠር ቀበሌያት ዐሥሩ ለተከታታይ ሦስት ዓመታት ዝናብ ያላገኙ በመሆኑ 58 ሺህ ያኽል ቤተሰቦች ለከፍተኛ የምግብ እህል እጥረት የተጋለጡና የእለት እርዳታ የሚሹ ሆነዋል፡፡ ም/አስተዳዳሪው ችግሩን ለማቅለል እስከ አሁን ከዞን፣ ከክልልና ከፌዴራል መንግሥት የምግብና የዘር እህሎች እንዲሁም «እኛው ለእኛው» በሚል መርሕ ከዞኑ ከፍተኛ አካባቢዎች በዝቅተኛ አካባቢ ለሚኖሩ ወገኖች ድጋፍ እየተደረገ ቢሆንም በቂ አይደለም ብለዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ላደረገው የምግብ እህል ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት ም/አስተዳዳሪው ወረዳው የገጠመውን ወቅታዊ ችግር ከመቅረፍ ባሻገር ለዘላቂ መፍትሔ ዩኒቨርሲቲው እንደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም በምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፎች በጋራ ቢሠራ ከፍተኛ ውጤት ሊያስገኝ የሚችል ተፈጥሯዊና ሌሎችም አመቺ ሁኔታዎች ያሉ በመሆኑ በቀጣይ በትኩረት እንዲሠራ ጠይቀዋል፡፡  

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት