በጫሞ ሐይቅ ረግረጋማ ስፍራና የሐይቁ የላይኛው ተፋሰስ አካል በሆነው ጌዣ ደን ውስጥ ምርምርን መሠረት ያደረገ የመልሶ ማልማት የሙከራ /Pilot/ ፕሮጀክት አካላዊና ሥነ-ሕይወታዊ ሥራዎች ተስፋ ሰጪ ውጤት እያሳዩ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ የሙከራ ፕሮጀክቱ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከሮማንና ኃይለማርያም ፋውንዴሽን፣ ከቤልጂየሙ ኬዩሊዩቨን ዩኒቨርሲቲ/KU Leuven University/ እና ቢኦኤስ+/BOS+/ ከተሰኘ ድርጅት ጋር በመተባበር የተጀመረ ሲሆን ከጀርመን ልማት ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ለሚሠራው ለአምስት ዓመታት የሚቆይ ፕሮጀክት እንደ ማሳያ የሚያገለግል ነው፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ከጫሞ ሐይቅ ጋር በተያያዘ ከአቅሙ በላይ መሰገሩና የሐይቁ በፈር ዞን/Buffer Zone/ ለእርሻ የተጋለጠ መሆን መሠረታዊ ችግሮች መሆናቸውን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ‹‹AMU-IUC›› ፕሮግራም ማኔጀርና የውኃ ሥነ-ምኅዳር ተመራማሪ ዶ/ር ፋሲል እሸቱ ይገልጻሉ፡፡ እንደ ዶ/ር ፋሲል የሐይቁ ረግረጋማ ቦታ/Wetland/ የሐይቁ የማጣሪያ አንዱ አካልና ዓሣዎች እንቁላላቸውን የሚጥሉበትና የሚራቡበት ቦታ ስለሆነ የሐይቁ ዳርቻ በረግረግና በዕፅዋት እንዲሞላና እንዲያገግም ሳይንሳዊ ጥናት ይፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ ረግረጋማ ስፍራውን መልሶ ለማልማትና ወደ ሐይቁ የሚገባውን ደለል ለመከላከል ‹‹AMU-IUC›› እና ‹‹ሌቶ ዓሣ አስጋሪዎች ማኅበር›› ለሠርቶ ማሳየነት በጋራ የተረከቡትን ሦስት ሄክታር መሬት ከሰው ንክኪ ነጻ በማድረግ የተሠራው ሥነ-ሕይወታዊ ሥራ አስደሳች ውጤት እያሳየ ነው፡፡ በረግረጋማ ስፍራው የተተከሉት የተሻለ የማጣራት አቅም ያላቸው ደንገልና ሶኬን ጨምሮ ከዚህ ቀደም ጠፍተው የነበሩ ዕፅዋት በጥሩ ሁኔታ እያደጉ ሲሆን በነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ የጠፉ የአእዋፍ ዝርያዎችም በአካባቢው መታየት ጀምረዋል፡፡

የሌቶ ዓሣ አስጋሪዎች ማኅበር አባል አቶ ደርሶ ደረሰ ባለፉት ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ስፍራው በእጅጉ ተጎድቶ ከነበረበት በጥሩ ሁኔታ ማገገሙንና የጠፉ ዕፅዋት፣ የሸሹ እንስሳትና አእዋፍ ዳግም መታየት መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ ወደ ስፍራው ለሚመጡ እንግዶች የምግብ አገልግሎት የሚያቀርበው ማኅበሩ ለስፍራው በባለቤትነት ስሜት እንክብካቤና ጥበቃ እንደሚያደርግና በታየው ለውጥ ደስተኛ መሆናቸውን አቶ ደርሶ ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል በጫሞ የላይኛው ተፋሰስ ውስጥ በሚገኘው የጌዣ ደን ለመንገድ ሥራ የተደረገው ቁፋሮ የፈጠረው ጎርጅ /Gully/ ለአፈር መሸርሸር ያጋለጠው ሲሆን ቀደም ሲል በጎርጁና በደኑ በፈር ዞን ከ‹‹GIZ›› ጋር በመተባበር የአፈር መከላከያ ግድብ /Brushwood check dam/ና የመሳሰሉ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት በደኑ ላይ ጥናት ሲያደርጉ የነበሩት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ሕይወት ት/ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር ሥዩም ጌታነህ በጥናት በቆዩባቸው ጊዜያት ውስጥ የአካባቢው ነዋሪ በደኑ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ በጣም አሳሳቢ መሆኑንና የደኑን መመናመን የሚያሳየውን የጥናት ውጤታቸውን ተከትሎ በትብብር በተገኘ ፈንድ ወደ መልሶ ማልማት ሥራ መግባታቸውን ይናገራሉ፡፡ በጣም የተመናመኑና ሊጠፉ የደረሱ የተፈጥሮ ዛፍ ዘሮችን መትከል እንዲሁም በደኑ ዙሪያ በፈር ዞኑን አጥሮ መልሶ እንዲያገግም ማድረግ በዋናነት የሚሠሩ ሥራዎች መሆናቸውን ዶ/ር ሥዩም ገልጸዋል፡፡ በደኑ ውስጥ በተፈጠረው ጎርጅ ላይ በእንጨትና በቀርከሃ እንዲሁም በአካባቢው በቀላሉ በሚገኙ ጽድና ትናንሽ እንጨቶች በሁለት ዓይነት መንገድ የአፈር መገደቢያው የተሠራ ሲሆን በመገደቢያው ውስጥ ከጥናቱ ጋር የተያያዙ የደጋ ግራር /Acacia decurrens/፣ ቀርከሃ /Yushania alpine/፣ ክትክታ/ Dodonaea angustifolia/፣ ኮርች/ Erythrina brucei/ እና የመኖ ሳር/ Elephant grass/ የመሳሰሉ ዕፅዋት እንዲሁም በደኑ ዙሪያ ባሉ የአርሶ አደር መሬቶችም እንደ አርሶ አደሮቹ ምርጫ የባሕር ዛፍና ሌሎች ችግኞች ተተክለዋል፡፡

እንደ ተመራማሪው ‹‹የደጋ ግራር›› በቶሎ የሚያድግና ሰፊ የመባዛት እድል ያለው ሲሆን ቅጠሎቹ ሲረግፉ በፍጥነት የመበስበስ ባሕርይ ያላቸውና የመሬት ለምነቱን የሚጨምሩ ናቸው፡፡ ከተክሉ ሥር የሚበቅሉት አራሙቻና ሌሎች ሀገር በቀል አረሞችም አፈሩን በደንብ ቆንጥጠው ይይዛሉ፡፡ እንደ ቀርከሃ ዓይነት ባሕርይ ያለውና ወደ ሸንኮራነት የሚያዘነብለው ‹‹የመኖ ሳር›› እየተቆረጠ በቀላሉ የሚራባና በታጨደ ቁጥር የሚበዛ ሲሆን አፈርና ውኃን ከመጠበቅ ባሻገር ለከብት መኖነትም ያገለግላል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ እየተቆረጠ በቀላሉ የሚጸድቀው ‹‹ኮርች›› መሬትን የመያዝ ኃይሉ ከፍተኛ ሲሆን ቅጠሉ በበጋም ሆነ በክረምት የከብቶች ተመራጭ ምግብ ነው፡፡ በሌላ በኩል በጣም በተራቆተና አፈሩ ፈጽሞ ተጠርጎ በኼደበት ቦታ ላይ የተተከለው ‹‹ክትክታ›› መሬቱ ካገገመ በኋላ በሌላ ዕፅዋት የሚተካ ይሆናል፡፡

መልክአ ምድሩ በአብዛኛው የላይኛው ከፍተኛ ቦታው ለአፈር መሸርሸር ሙሉ በሙሉ የተጋለጠ በመሆኑ የአካላዊና ሥነ-ሕይወታዊ ሥራው ውኃው ወደ መሬት እንዲሰርግ የሚያደርግና አፈሩን የሚይዝ ነው ያሉት ተመራማሪው ከላይ ተንደርድሮ በሚወርደው ውኃና ደለል ምክንያት በታችኛው የመሬት ክፍል/lowland/ ላይ የሚደርሱ የደለልና የጎርፍ አደጋዎች እንዲቀንሱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ወደ ጫሞ ሐይቅ የሚገባው ደለል በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስና የአርባ ምንጭ ከተማ መለያ የሆኑት ምንጮች እንዲጎለብቱ የሚያደርግ ነው፡፡ ዶ/ር ሥዩም ሥራውም ሆነ የሚያስገኘው ጥቅም እጅግ ሰፊ መሆኑን ጠቅሰው ጅምርና እንደ ማስተማሪያ የሚታይ በመሆኑ ተሞክሮውን በማየት ማኅበረሰቡም ሆነ ሌሎች አካላት በየአካባቢያቸውም ሆነ በየማሳዎቻቸው ቢተገብሩት ከፍተኛ የአካባቢ ጥበቃ ለውጥ የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በገረሴ ከተማ አስተዳደር የግብርና ዩኒት መሪና የደን ኤክስፐርት አቶ ደስታ ጉዲሳ ቀደም ሲል በጌዣ ደን ውስጥ ጎርጁን ተከትሎ በተሠራው የክትር ሥራ ታጥቦ ይኼድ የነበረው አፈር መቆሙንና በግድቡ ውስጥ የተተከሉት ዕፅዋት በጥሩ ሁኔታ ጸድቀው አፈሩን መያዝ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ ማኅበረሰቡ በሚታየው ለውጥ ደስተኛ ነው ያሉት አቶ ደስታ የአካላዊና ሥነ-ሕይወታዊ ሥራውን በየማሳዎቻቸው ለመተግበር ፍላጎት ማሳደራቸውንና ቀርከሃና የደጋ ግራሩን መትከል የጀመሩ እንዳሉም ጠቁመዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት