የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ፈረንሳይ ሀገር ከሚገኝ "Fund for Innovative Development (FID)" ድርጅት ጋር በመተባበር "Adoption of Rhizobium Inoculant Technology (ARIT)" የተሰኘ የትብብር ፕሮጀክት የተፈጥሮ ማዳበሪያ "Bio-Fertilizer" ማምረት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ የባዮሎጂ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር አሽናፊ ኃይሉ ለተፈጥሮ ማዳበሪያነት የሚያገለግል ንጥረ ነገር ዩሪያ/Urea/ በአፈር ባክቴሪያዎች የሚመረትበትን ደረጃ በመለየት ለማሳውና ለጥራጥሬው ዓይነት አስፈላጊ የሆነ የተፈጥሮ ማዳበሪያን በማምረት ማሠራጨት ወይም የተፈጥሮ ማዳበሪያን ተቀብሎ አለማምዶ ማሠራጨት የፕሮጀክቱ ትኩረት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በስምንት ጥራጥሬ እህሎች ማለትም ባቄላ፣ አተር፣ ሽምብራ፣ ኦቾሎኒ፣ አኩሪ አተር፣ የእርግብ አተር፣ ጓያና ማሾ ላይ እየሠራ ሲሆን የኬሚካል ማዳበሪያ ገዝተው መጠቀም የማይችሉ 220 አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡

ለፕሮጀክቱ ትግበራ €50,000.00 /ሃምሳ ሺህ ዩሮ/ ወይም 2.75 ሚሊየን ብር በጀት መመደቡን የገለጹት ዶ/ር አሸናፊ ፕሮጀክቱ ከተጀመረ አንድ ዓመት የሞላውና የአንድ ዓመት የትግበራ ጊዜ የሚቀረው ሲሆን ለአንድ 3ኛ እና ለሁለት 2ኛ ዲግሪ ተማሪዎች የገንዘብ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ፐሮጀክቱ የተፈጥሮ ማዳበሪያን ለማምረት መነሻ የሆኑ የአፈር ባክቴሪያዎችን ልየታ በማድረግ በጋሞ፣ ጎፋ፣ ኮንሶና ደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም ደራሼ፣ ቡርጂና አሌ ልዩ ወረዳዎች ለተለዩ አርሶ አደሮች ለማደረስ እየሠራ ነው።

በኮሌጁ የባዮ-ቴክኖሎጂ የ3ኛ ዲግሪ ተማሪና እጩ ዶ/ር መሠረት መለሰ በፕሮጀክቱ የተጀመረው የምርምር ሥራ ለኮሌጁ የመጀመሪያው መሆኑን ጠቅሶ የቤተ-ሙከራ ዕቃዎች፣ ኬሚካልና ሪኤጀንቶች በፕሮጀክቱ አማካኝነት የተሟሉ መሆኑን ገልጿል፡፡

በአፈር ባክቴሪያ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማምረት የሚሠራው ፕሮጀክት ለትምህርታቸው እውቀትና ክሂሎት እንዲያገኝ እንደረዳውም እጩ ዶ/ር መሠረት ተናግሯል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት