አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከባዮ እና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትና ሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር ‹‹ወደ ዓለም አቀፍ የተመጣጠነ ምግብ ደኅንነት/Towards Global Food and Nutrition Security›› በሚል መሪ ቃል ያዘጋጀው የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የእንሰት ሲምፖዚዬም ከጳጉሜ 1-2/2015 ዓ/ም የተለያዩ መርሃ ግብሮችን በማከናወን ተጠናቋል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊና የሲምፖዚዬሙ የክብር እንግዳ አቶ ዑስማን ሱሩር ለምግብነት፣ ለመድኃኒትነት፣ ለእንስሳት መኖነት፣ ለአካባቢ ጥበቃና ለድርቅ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚሰጠው እንሰት የአገልግሎቱን ያህል በቂ ትኩረት አላገኘም ብለዋል፡፡ እንደ ኃላፊው ከመማር ማስተማር ሥራ ባሻገር ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ምርምሮችን የሚያካሂዱ የከፍተኛ ትምህርትና ምርምር ተቋማት፣ የግብርና ዘርፍ ባለድርሻ አካላትና ሌሎችም ተክሉ የሚገባውን ትኩረት አግኝቶ ሀገሪቱ ለያዘችው የምግብ ዋስትና ማረጋገጥና የድኅነት ቅነሳ ጉዞ የላቀ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የበኩላቸውን ግዴታ ልወጡ ይገባቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የወሰደው ቀዳሚ እርምጃ የሚበረታታና አርአያ የሚሆን ነው ያሉት አቶ ዑስማን ኃላፊነቱን በጋራ ለመወጣት የተለያዩ ተቋማትና አጋር ድርጅቶች በጥምረት ለመሥራት እንዲችሉ መድረኩ ዕድል የሚሰጥ ነውም ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ፕሬዝደንት አምባሳደር ፕ/ር አድማሱ ፀጋዬ ባቀረቡት ቁልፍ መልእክት እንተናገሩት የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋመውና ሚሊዮኖችን መመገብ የሚችለው እንሰት የግብርና መስክ ሀብት የሆነ ሰብል ቢሆንም የሚገባውን ዕውቅናና ትኩረት አላገኘም፡፡ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ካለባቸው 119 የዓለም ሀገራት ኢትዮጵያ 104ውን ደረጃ መያዟን የጠቆሙት አምባሳደሩ ዓመቱን ሙሉ ሊመረትና ምርቱም ያለ ብክነት ለረዥም ጊዜ ሊቀመጥ የሚችለው እንሰት በአግባቡ ከተሠራበት በቀጣዮቹ ዓመታት የምግብ ዋስትናችን ተስፋ የሚሆን ልዕለ ምግብ ነው ብለዋል፡

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ ዩኒቨርሲቲው በምርምር ዘርፍ ቅድሚያ ሰጥቶ ከሚሠራባቸው ርእሰ ጉዳዮች አንዱ እንሰት መሆኑን ጠቁመው የአመራረት ሂደቱን በማሻሻል ከተክሉ የሚገኘውን ጥቅም ለማስፋትና በሥራው ላይ የሚሳተፉ በተለይም ሴቶች የሚደርስባቸውን ድካምና ሌሎች ጉዳቶች ለማስቀረት ብሎም እንሰት በምግብ ዋስትና በኩል ከአካባቢው አልፎ ዓለም የሚጠቀምበት እንዲሆን ዩኒቨርሲቲው በርካታ ምርምሮችንና የትብብር ፕሮጀክቶችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የባዮቴክኖሎጂ ተመራማሪና የእንሰት ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ እንደገለጹት በባህላዊ መንገድ ሲሠራ ጊዜና ጉልበት የሚፈጅ፣ ለጤና ችግሮች የሚያጋልጥ፣ የምርት ጥራት ላይ ችግር የሚያስከትልና ለብክነት የሚያጋልጠውን የእንሰት መፋቅና ማብላላት ሂደት ለማዘመን ዩኒቨርሲቲው በርካታ ምርምሮችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዚህም ሂደቱን የሚያሻሽሉ ዘመናዊ የእንሰት ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂዎችንና የማብላላት ሂደቱን የሚያፋጥን እርሾ እንዲሁም እሴት የተጨመረባቸው ኩኪስ፣ ኬክ፣ ዳቦና ሌሎችንም  ምግቦች በማዘጋጀት ለማኅበረሰቡ ለማስተዋወቅ ተችሏል ብለዋል፡፡ ቴክኖሎጂዎቹን በኢትዮጵያ እንሰት አብቃይ ለሆኑ አካባቢዎች ብሎም ከሀገር ውጪ ለማስተዋወቅና ኅብረተሰቡን በሰፊው ተጠቃሚ ለማድረግ ጅምር ሥራዎች ያሉ ሲሆን በቀጣይ ከአጋር አካላት ጋር በተሻለ ትብብር መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ዶ/ር አዲሱ ገልጸዋል፡፡

የ‹‹Alabaster International›› መሥራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሚስስ ሻኖን ሩቤራ/Mrs Shannon Rubera/ የተመጣጠነ ምግብ የዓለም በተለይም የአፍሪካ ትልቅ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው እንሰትና የመሳሳሉ ድርቅን የሚቋቋሙ ሰብሎች ላይ በጋራ መሥራት አስፈላጊ በመሆኑ ተቋማቸው በኢትዮጵያ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና ከኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እንዲሁም ከኬንያዎቹ ጆሞ ኬኒያታ የግብርናና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ/ Jomo Kenyatta University of Agriculture and Technology/ እና የሴት ሕፃናት ኔትወርክ/Girl Child Network/ ጋር በእንሰት ላይ በጋራ ለመሥራት በቅርቡ ስምምነት መፈራረሙን ተናግረዋል፡፡

በሲምፖዚዬሙ ለውይይት መነሻ የሚሆኑ ጽሑፎች ከተለያዩ ተቋማት በመጡ ባለሙዎችና የሥራ ኃላፊዎች የቀረቡ ሲሆን አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከባሕር ዳር፣ ደብረ ማርቆስ እና ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በእንሰት እና ሞሪንጋ ላይ ምርምር ለማድረግና ለማስተዋወቅ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል። የመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች በዶርዜ አካባቢ ተገኝተው ባህላዊውን የእንሰት አፋፋቅና ማብላላት ሂደት እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ያደራጀውን ሞዴል የእንሰት ማቀነባበሪያና ሞዴል የእንሰት ማባዣ ጣቢያ የጎበኙ ሲሆን ባህላዊው አሠራር ምን ያህል አድካሚ መሆኑንና ዩኒቨርሲቲው በመስኩ የሚያስመሰግን ሥራ ማከናወኑን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ቴክኖሎጂዎቹንና ሌሎች የምርምር ሂደቶችን አስመልክቶ ቢሻሻሉ የበለጠ መልካም ሥራ ለመሥራት ያግዛሉ ያሏቸውን ጥቆማዎችና በጋራ ለመሥራት ያላቸውን ፍላጎትም አቅርበዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ዩኒቨርሲቲው እንሰትን ጨምሮ ሌሎች የደጋ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የቆላ ሰብሎች ያሉበት አካባቢ መገኘቱን እንደ ዕድል ተጠቅሞ ባሉት የምርምርና ሥልጠና ማዕከላት ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ምርምሮችን እያካሄደ መሆኑን ጠቅሰው የተፈጠሩ ትብብሮችና ከሲምፖዚዬሙ ተሳታፊዎች የተገኙ በርካታ ገንቢ አስተያየቶች ለቀጣይ ሥራ እድገትና ስኬት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት