የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ እና አርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል አውስትራሊያ ሀገር ከሚገኘው ‹‹Menzies School of Health Research›› ከተሰኘ የጤና ምርምር ት/ቤት ጋር በመተባበር በሚያከናውኑት  የጥናት ውጤት ላይ ግምገማዊ ወርክሾፕ መስከረም 8/2016 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስክዩቲቨ ዳይሬክተር እና በኢትዮጵያ የጥናቱ ዋና ተመራማሪ ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ እንደገለፁት የምርምር ፕሮጀክቱ በዋናነት ቫይቫክስ ተብሎ ለሚጠራው የወባ በሽታ ዓይነት የሚሰጡ መድኃኒቶችን ውጤታማነት፣ ፈዋሽነትና የጎንዮሽ ጉዳቶችን መፈተሽን ዓላማ በማድረግ በሁለት ቡድን በተከፈሉ 350 የፋልስፋረም ወባ ታማሚዎች  ላይ ለ63 ቀናት ህክምናና ክትትል የተደረገበት ነበር፡፡ የፋልሲፓረም ወባ ታማሚዎች ከታከሙ በኋላ ቫይቫክስ የተሰኘው የወባ በሽታ ዓይነት በጉበት ውስጥ ተደብቆ በመቆየት በአዲስ መልክ የሚያገረሽ በመሆኑ ይህን ለመከላከል በጉበት ውስጥ ለረጅም ጊዜ የሚቆየውን ቫይቫክስ የተሰኘውን የወባ በሽታ ማጥፋት የሚችለውን ፕሪማክዊን/Primaquine/ የተባለውን  መድኃኒት  በሁለት መንገድ ማለትም የአንድ ቀን ዝቅተኛ መጠን እና የአሥራ አራት ቀናት ከፍተኛ መጠን ለታማሚዎች በመስጠትና ክትትል በማድረግ የትኛው  ዘዴ ይበልጥ ውጤታማ እንደሆነና ዳግም በሽታው በጉበት ውስጥ ተደብቆ እንዳይነሳ የማድረግ አቅም እንዳለው መለየት የጥናቱ ዋነኛ ትኩረት እንደነበር ዶ/ር ታምሩ አውስተዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ታምሩ ገለፃ ለሰባት ቀን የሚሰጠው ዘዴ ቫይቫክስ ወባ በአምስት እጥፍ በድጋሚ ያላገረሸ መሆኑንና ለፋልሲፓረም ታካሚምዎችም  ጭምር  የተሻለ ለውጥ ማምጣቱን የምርምር ቡድኑ አረጋግጧል፡፡

አውስትራሊያ ሀገር ከሚገኘው ‹‹Menzies School of Health Research›› ተቋም የመጡት ዋና ተመራማሪ ተባባሪ ፕ/ር /Assoc.Prof./ ካማላ ቲሪመር (Kamala Thriemer) የምርምር ሥራው የተካሄደው በባንግላዲሽ፣ በኢንዶኔዥያና ኢትዮጵያ ሲሆን በኢትዮጵያ የተደረገው ጥናት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና አርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ጋር በትብብር የተካሄደ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በአርባ ምንጭ በተካሄደው የመድኃኒት ውጤታማነት ፍተሻ ጥናት 350 ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን ይህም በሌሎች ሀገራት ከተካሄደው ጥናት በጥናቱ ተሳታፊዎች ቁጥር ከፍተኛው ያደርገዋል ብለዋል፡፡ በሶስቱም ሀገራት በተደረጉት ጥናቶች የተገኙ ውጤቶች በሽታውን የማከም ውጤታማነትን የሚያሻሽሉ መሆናቸውን  ተባባሪ ፕሮፌሰሯ ገልጸዋል፡፡ ጥናቱ በስኬት እንዲጠናቀቅ በርካታ አካላት የበኩላቸውን ሚና በአግባቡ መወጣታቸውን በመጥቀስ በተለይ በሥራው ላይ ለተሳተፉ የጥናት ቡድኑ አባላት ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የጥናቱ ተሳታፊ አቶ ስለሺ እንዳለ እንደገለፁት አሁን ላይ ወባ በጣም የተቸገርንበት በሽታ ሲሆን ጥናቱ ላይ የመሳተፍ ዕድሉን በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልፀዋል፡፡ መጀመሪያ ጥናቱ ላይ ሲሳተፉ የ14 ቀን መድኃኒት መውሰዳቸውን የገለጹት አቶ ስለሺ ከወር በኋላ ድጋሚ በበሽታው እንደተያዙና የሰባት ቀን መድኃኒቱን ከወሰዱ በኋላ ግን ትልቅ ለውጥ ማየታቸውን ተናግረዋል፡፡ አክለውም እንደዚህ ዓይነት ችግር ፈቺ ጥናቶች አሁን ላይ እየተቸገርን ላለንባቸው እንደ ታይፈስና ታይፎይድ  ባሉ በሽታዎች ላይም ቢደረጉ የተሻለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ሌላኛዋ የጥናቱ ተሳታፊ ወ/ሪት ሊያ አየለ እንደገለችው ከዚህ ቀደም ወባ በተደጋጋሚ እንደሚይዛት ተናግራ አሁን ላይ በጥናቱ የተረጋገጠውን የሰባት ቀን መድኃኒት በመውሰዷ ከፍተኛ ለውጥ ማየቷን ተናግራለች፡፡ በቀጣይ መሰል ጥናቶች በሌሎች በሽታዎችም ላይ ቢሠሩ ለማኅበረሰቡ እጅግ ጠቃሚ እንደሚሆን ሃሳቧን ሰጥታለች፡፡

በወርክሾፑ ካማላ ቲሪመር/ተባ/ፕ/ር (Kamala Thriemer Assoc. Prof.) አውስትራሊያ ሀገር ከሚገኘው ‹‹Menzies School of Health Research›› ተቋም፣ የዩኒቨርሲቲው የምርምር ኤክስክዩቲቨ ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀብተማርያም፣ በምርምሩ የተሳተፉ  ሐኪሞችና የጤና ባለሙያዎች፣ ከኮሌጁ የመጡ ባለሙያዎች፣ መድኃኒቱን ተጠቅመው ለውጥ ያመጡ የምርምሩ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት