አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሠለጠናቸውን በድኅረ ምረቃ በሦስተኛ ዲግሪ ሦስት፣ በሁለተኛ  ዲግሪ 121 እና በቅድመ ምረቃ 1,348 እንዲሁም በፒጂዲቲ ሦስት በአጠቃላይ 1,475 የ36 ባች ተማሪዎችን ለሁለተኛ ዙር መስከረም 12/2016 ዓ/ም አስመርቋል፡፡ ከተመራቂዎቹ መካከል 395ቱ ሴቶች ናቸው፡፡  ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ የአካዳሚክ ጉዳች ዋና ሥራ አስፈጻሚና የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር ኤባ ሚጀና በሀገራችን ኢትዮጵያ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማረጋጥና ሠላምና ዴሞክራሲን ለማጎልበት ትምህርት ቁልፍ መሣሪያ መሆኑን በውል በመገንዘብ አግባብነትና ጥራት ላለው ትምህርት በተለይም ለትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ተደራሽነትና ፍትሃዊነት ልዩ ትኩረት በመስጠት መንግሥት በልዩ ትኩረት እየሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡ ምሩቃን በትምህርት ቆይታቸው ባገኙት ዕውቀትና ልምድ የራሳቸው፣ የቤተሰቦቻቸውን የሀገራቸውን ማኅበረሰብ ለመለወጥ የበኩላቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ይወጡ ዘንድ አሳስበው ሥራ ፈጣሪ በመሆን፣ ዕውቀታቸውን በተግባር በመተርጎምና የሕይወት ፈተናዎችን በድል በማለፍ የበለጠ ለማወቅና በየጊዜው የተሻለ ሰው ለመሆን መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እስከ አሁን ድረስ ለ36 ዙሮች ተማሪዎችን አሠልጥኖ ሲያስመርቅ የቆየ ሲሆን የ36ው ባች 2 ዙር ተመራቂዎችን ጨምሮ በልዩ ልዩ መስኮች ከ78 ሺህ በላይ ምሩቃንን በማፍራት ለሀገሪቱ የሰው ሀብት ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል፡፡ ተመራቂ ተማሪዎች በቆይታቸው ባካበቱት ዕውቀትና ክሂሎት በአብሮነት ተባብሮ የመኖርና የመሥራት ባህልን በመጠቀም ራሳቸውን፣ ወገናቸውንና ሀገራቸውን በሚያሳድጉ ተግባራት ላይ በርትተው እንዲሠሩ ፕሬዝደንቱ አሳስበዋል፡፡ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ በሁሉም የትምህርት መስኮች የተተገበረውን የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርት ማጠናቀቂያ የመውጫ ፈተና ተቀብለው ያለፉ ተመራቂዎች ምረቃ መሆኑ ምረቃውን ልዩ እንደሚያደርገው ዶ/ር ዳምጠው ገልጸዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ምሩቃን /አሉምናይ/ ማኅበር ጸሐፊ ጋዜጠኛ ሣልሳዊት ባይነሳኝ በትምህርት ሂደት ውስጥ ብዙ ውጣ ውረዶች ቢኖሩም ጠንክረን በመሥራት ለስኬት መብቃትና የደረስንበትን ስኬት አክብረን በመቀበል ለተሻለ ነገር ራስን ማዘጋጀትና መሥራት እንደሚገባ ገልጸው ምሩቃን የኅብረቱ አባል ሆነው ከሌሎች ምሩቃን ጋር እንዲሠሩና ለተማሩበት ዩኒቨርሲቲ፣ ለአካባቢው ማኅበረሰብና ለመላው የሀገራችን ሕዝቦች ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦ ማበርከት እንዲችሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከአጠቃላይ ሴት ተመራቂዎች መካከል ተማሪ ዲያና ብርሃኑ ከአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት 3.35፣ ተማሪ ኤደን ሞገስ ከአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት 3.79፣ ተማሪ ቤተልሄም ነጋሽ ከተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ 3.73፣ ተማሪ ቁም ነገር ተመስገን ከግብርና ሳይንስ ኮሌጅ 3.61፣ ተማሪ ሱመያ ፈቲ ከቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ 3.96፣ ተማሪ ኩሌኒ ኢፋ ከማኅበራዊ ሳይንስና ሥነሰብ ኮሌጅ 3.68፣ ተማሪ ትዕግስት አቦዬ ከሥነትምህርትና ሥነባህርይ ት/ቤት፣ 3.48፣  በማስመዝገብ ልዩ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

ከተመራቂዎቹ መካከል ተማሪ ባዩ አለኸኝ ከአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት 3.44፣ ተማሪ ልዑል ስንታየሁ ከአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት 3.97፣ ብዙአየሁ አለኸኝ ከተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ 3.97፣ ተማሪ ካቦ ከተቦ ከግብርና ሳይንስ ኮሌጅ 3.93፣ ተማሪ አላዛር ቅጣው ከብዝነስነ ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ 3.99፣ ታዘዘ አያሌው ከማኅበራዊ ሳይንስና ሥነሰብ ኮሌጅ 3.90፣ ተማሪ ኃይለየሱስ ደምሴ ከሥነትምህርትና ሥነባህሪ ት/ቤት 3.79 በማምጣት የወርቅ ሜዳልያ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

ዶ/ር ጳውሎስ ታደሰ ከተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ እና ዶ/ር ተሾመ ይርጉ ከማኅበራዊ ሳይንስና ሥነሰብ ኮሌጅ ላገኙት የሙሉ ፕሮፌሰርነት አካዳሚክ ማዕረግ ዕድገት እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የሬጂስትራርና አሉምናይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ማሌቦ ማንቻ የተመራቂዎችን መረጃ ያቀረቡ ሲሆን የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ ተመራቂዎችን ለምረቃ አቅርበው አስመርቀዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት