የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ምርምር ማዕከል ጨንቻ በሚገኘው ግርጫ የደጋ ፍራፍሬና አትክልት ምርምር ማዕከል ቅጥር ግቢ ውስጥ ዘመናዊ የወተት ላሞች እርባታ ጣቢያ /Dairy Farm/ እያስገነባ ይገኛል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ ሀገራችን ኢትዮጵያ ባላት የእንስሳት ሀብት በአፍሪካ ከቀዳሚዎቹ ተርታ የምትሰለፍ ብትሆንም ሀገሪቱም ሆነ ማኅበረሰቡ ከመስኩ ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም እያገኙ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ግርጫ ላይ እየተሠራ የሚገኘው የወተት ላሞች እርባታ ጣቢያ ዋነኛ ዓላማ የተሻሻሉና ከፍተኛ የወተት ምርት የሚሰጡ ዝርያዎችን በማምጣትና በማዳቀል የተሻሉትን ለማኅበረሰቡ በማሰራጨት የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሆነ ም/ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡

የምርምር ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀብተማርያም እንደገለጹት ከተቋቋመ ረዥም ጊዜ ያስቆጠረው የዩኒቨርሲቲው የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ምርምር ማዕከል በምርምር፣ በማኅበረሰብ ጉድኝትና በተግባር ትምህርት እንዲሁም ከገቢ አንጻር ተቋሙን የሚደጉሙ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡ ማዕከሉ አርባ ምንጭ ላይ የከብት ድለባ ሥራ እየሠራ ሲሆን በዋናው ግቢ በተቋቋመው የዶሮ እርባታ ማዕከል የሥጋ እና እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን እያረባ ይገኛል፡፡ በማዕከሉ ከሥጋ ዶሮዎች ባሻገር በየሳምንቱ ከሁለት ሺህ በላይ እንቁላል ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ እያቀረበ እንደሚገኝም ዶ/ር ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡ ግርጫ ላይ እየተሠራ የሚገኘውን የወተት ላሞች እርባታ ጣቢያ ከሦስት እስከ አራት ወራት ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ወደ ሥራ ለማስገባት መታቀዱን ዶ/ር ተስፋዬ ጠቁመዋል፡፡

የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አቶ እሳቱ በቀለ በበኩላቸው የወተት ላሞች እርባታ ጣቢያው ሥራ ሲጀምር ምርምሮች የሚሠሩበት፣ አዳዲስ የወተት ላም ዝርያዎች እና ቴክኖሎጂዎች ለማኅበረሰቡ የሚተዋወቁበት፣ ሥልጠናዎች የሚሰጡበት እንዲሁም ተማሪዎች የሚማሩበት ስፍራ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

የፕሮጀክቱን ዲዛይን የሠሩት የዩኒቨርሲቲው የአርክቴክቸርና ከተማ ፕላን ፋከልቲ መምህር ዳግም ፈቃዱ የዲዛይን ሥራው የወተት ላሞችን አኗኗር፣ የአካባቢውን የአየር ሁኔታ እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ዓለም አቀፍ የመስኩን ስታንዳርዶች መሠረት በማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ አርክቴክቱ ገለጻ በዲዛይን ሥራው ላይ የከብቶቹ ጤናና ምቾት ልዩ ትኩረት የተሰጠው ሲሆን 100 የሚታለቡ የወተት ላሞችን መያዝ ከሚችለው ዋናው ሼድ ባሻገር የታመሙ ከብቶች፣ አዲስ የተወለዱ ጥጆችና ወላድ ላሞች ለብቻ የሚሆኑበት ሼድ ሌላኛው የዲዛይኑ አካል መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የግንባታ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ባለሙያና የፕሮጀክቱን ኮንትራት አስተዳደርና ዲዛይን እየተከታተሉ የሚገኙት አርክቴክት እሱባለው ሳሙኤል አጠቃላይ ፕሮጀክቱ በ10 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ላይ የሚያርፍ፣ 10 ብሎኮች ያሉትና ደረጃ በደረጃ የሚገነባ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዋናው ሼድ፣ የአስተዳደርና የወተት ማቀነባበሪያ ዩኒት፣ የታመሙ፣ አዲስ የተወለዱ ጥጆችና በሬዎች ሼድ፣ የደረቅ መኖ ማከማቻ ሼድ፣ የባዮጋዝ ዳይጀስተር እና ሌሎችም በግንባታ ፕሮጀክቱ ከተካተቱ ሥራዎች መካከል የሚጠቀሱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ከተጀመረ አጭር ጊዜ እንደሆነው የገለጹት አርክቴክቱ አሁን ላይ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም 30 በመቶ መድረሱንም አክለዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ግንባታ ተቆጣጣሪ መኃንዲስ የሆኑት አቶ ዓለማየሁ ስዩም በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ለዩኒቨርሲቲውም ሆነ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ የሚኖረው ሲሆን ግንባታው በታቀደው መሠረት በአጭር ጊዜ ውስጥ በጥራት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ቁጥጥርና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት