ወቅታዊውን የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ አስመልክቶ ‹‹የባሕር በር የልማት በር›› በሚል ርእስ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ታኅሣሥ 12/2016 ዓ/ም የፓናል ውይይት አዘጋጅቷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም እንደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ዕውቀት ከማመንጨትና ማስተላለፍ ጋር በማያያዝ በትላልቅ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ምክክር በማካሄድ ምሁራዊ አስተያየቶችና ምክረ ሃሳቦችን ሲያቀርብና በሚካሄዱ ጥናቶች ላይ ሲሳተፍ ቆይቷል፡፡ እንደ ፕሬዝደንቱ ‹የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ እንዴት ምላሽ ያግኝ?› የሚለው ጉዳይ ሰፊ የሆነ የምሁራንና የሕዝቡን ውይይት የሚጠይቅ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው ያዘጋጀው  መድረክም ታሪካዊ መሠረቶች፣ ዓለም አቀፍ ሕጎችና ጂኦፖለቲካዊ ሁኔታዎችን መሠረት በማድረግ አማራጭ የመፍትሔ ሃሳቦችን ለማግኘት ይረዳል፡፡

በውይይት መድረኩ ‹‹የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከጋራ ተጠቃሚነት አንጻር፡ ምጣኔ ሀብታዊ ዕይታ››፣ ‹‹የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከዓለም አቀፍ ሕግ አንጻር››፣ ‹‹የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ አመክንዮዎች፣ ተግዳሮቶች እና አማራጮች ከጂኦፖለቲካዊና የውጭ ግንኙነት ዕይታ አንጻር›› እና ‹‹የውጭ ኃይሎች በቀይ ባሕር አካባቢ ያላቸው አዳዲስ ፍላጎቶችና ፉክክር ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ያለው አንድምታ›› በሚሉ ርእሶች የውይይት መነሻ ጽሑፎች የዩኒቨርሲቲው መምህራን በሆኑት ዶ/ር መስፍን መንዛ፣ አቶ ዘርይሁን ቦዴ፣ አቶ ዓባይ ወርቁና አቶ ሙሴ ገ/እግዚአብሔር የቀረቡ ሲሆን የፓናል ውይይቱን የውኃ ምኅንድስና መምህርና ተመራማሪው ዶ/ር አብደላ ከማል መርተዋል፡፡

በጽሑፎቹ እንደተመለከተው የባሕር በር የነበራት፣ በታሪክ አጋጣሚ ባለቤትነቷን ያጣችውና ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነውን የወጭና ገቢ ንግዷን በጅቡቲ በኩል የምታከናውነው ሀገራችን ኢትዮጵያ ለከፍተኛ የወደብ ኪራይ፣ የገበያ ዋጋ ንረት፣ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ጥራታቸውን ጠብቀው በወቅቱ አለመድረስ፣ በዓለም አቀፍ ንግድ ተወዳዳሪ አለመሆንና ሌሎችም ኢኮኖሚያዊና ጂኦፖለቲካዊ ጫናዎችን አሳድሮባታል፡፡

እንደ ጥናት አቅራቢዎቹ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የሎጅስቲክ ወጭን በማቃለል የዘርፉን ተጠቃሚነት ከማሳደግ ባሻገር ከኢትዮጵያ መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ አንጻር ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ ጥያቄው ዛሬ ያልጀመረና ቀደም ሲልም ሲነሳ የቆየ ብሎም ተገቢና ዓለም አቀፍ መርህን የተከተለ ሲሆን ተፈጻሚነቱ የሰጥቶ መቀበል መርህን በመከተል የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገ ዲፕሎማሲያዊ አካሄድን ይጠይቃል፡፡ ከዓለም አቀፍ ሕግ አንጻር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በወጣው ኮንቬንሽን መሠረት የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት የባሕር መተላለፊያ በር የማግኘት መብት ያላቸው ሲሆን ኮንቬንሽኑ ተግባራዊ የሚሆነው በሀገራት መካከል በሚደረግ ስምምነት መሠረት ነው፡፡ አሁን ላይ በተለይም በቀይ ባሕር አካባቢ የውጭ ኃይሎች አዳዲስ ፍላጎቶችንና ከፍተኛ ፉክክር እያሳዩ ሲሆን ሀገራችን ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ አማራጮችን ተጠቅማ ለባሕር በር ጥያቄዋ ምላሽ በማግኘት ለቀጠናው ሀገሮች ከስጋት ይልቅ ኩራት የምትሆንበትን አቅም መገንባት ይጠበቅባታል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በአስተያየቶቻቸው የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ተገቢነቱ የማያጠያይቅና አዎንታዊ ምላሽ ቢያገኝ ከፍተኛ ሀገራዊ ፋይዳ የሚኖረው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ጉዳዩን አስመልክቶ ከምሁራን ባሻገር ሰፊው ሕዝብ የጋራ ግንዛቤ እንዲጨብጥ ማድረግ፣ ውስጣዊ የሀገር ሰላምና አንድነትን ማስጠበቅ፣ የመንግሥት አመራሮች በሚዲያዎች በሚሰጧቸው መግለጫዎችና ቃለ ምልልሶች ጥንቃቄ ማድረግ እንዲሁም ስልታዊና ሰላማዊ አካሄዶችን ተከትሎ ከፍጻሜ ለማድረስ መሥራት ይገባልም ብለዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት