የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቅጥር ግቢ እየተከናወኑ የሚገኙ የከተማ ግብርና ሥራዎችን ታኅሣሥ 15/2016 ዓ/ም ጎብኝተዋል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የኮሌጁ ም/ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ኤልያስ ልዬ እንደገለጹት ሥራው በ2015 ዓ/ም የጓሮ አትክልቶችን በማልማት የተጀመረ ሲሆን በ2016 ዓ/ም ሥራውን በማስፋት በቆሎ፣ ሙዝና ሽምብራ እየለማ ይገኛል፡፡ ለምርት የደረሱ የግብርና ውጤቶችን ለግቢው ማኅበረሰብ በቅናሽ ዋጋ በማቅረብ ገቢ ማግኘት መቻሉን የገለጹት አቶ ኤልያስ ሥራው ከገቢ ባሻገር ካምፓሱን ውብና ማራኪ እንዲሆን ያስቻለ ነው ብለዋል፡፡ አቶ ኤልያስ በቀጣይ ጊዜያት ሥራውን የማስፋፋት ዕቅድ መኖሩን ጠቁመው ለዚህም በካምፓሱ የተቆፈረው የጉድጓድ ውኃ ወደ ሥራ እንዲገባ ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጣው ዳርዛ ነጭ ሳር ካምፓስ በዩኒቨርሲቲው ከሚገኙ ካምፓሶች መካከል አነስተኛ የመሬት ስፋት ያለው ቢሆንም ያለውን ውስን መሬትና ክፍት ቦታ በዚህ መጠን አልምቶ ማየታቸው በእጅጉ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡ በየካምፓሱ የሚከናወኑ መሰል የከተማ ግብርና ሥራዎች ዩኒቨርሲቲውን ምቹ፣ ውብና ማራኪ በማድረግ የተቋሙን ማኅበረሰብ ለተሻለ ሥራ ከማነሳሳታቸው ባሻገር የተቋሙን የውስጥ ገቢ ለማሳደግ ጉልህ ሚና የሚጫወቱ መሆኑን ዶ/ር ዳምጠው አውስተዋል፡፡ መሰል ሥራዎችን የማከናወን ጅምሮች ዩኒቨርሲቲው ባሉት ሌሎች ካምፓሶችም እየተከናወኑ ይገኛሉ ያሉት ፕሬዝደንቱ በተለይ ሰፋፊ ክፍት መሬት ያላቸው ካምፓሶች ከነጭ ሳር ካምፓስ ልምድ እንዲወስዱ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በጉብኝት መርሃ ግብሩ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ፣ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ፣ የአስተዳደርና ልማት ም/ፕሬዝደንት ወ/ሮ ታሪኳ ወ/መድኅን፣ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ሽብሩና ሌሎች የካምፓሱ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት