ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ መምህራንና ተመራማሪዎች የ2030 የምርምር ትኩረት ዓለም አቀፍ የፕሮጀክት አጻጻፍን አስመልክቶ ከታኅሣሥ 22-24/2016 ዓ/ም ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ ሥልጠናው ዓለም አቀፍ የፕሮጀክት አጻጻፍ ስልቶች ምንነት፣ የፕሮጀክት አጻጻፍ ሂደትን መገምገም፣ የእድገት ጽንሰ ሃሳብ እንዲሁም ዘላቂ የልማት ግቦች አተገባበር ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ደግፌ አሰፋ እንደገለጹት የ2030 የምርምር ትኩረት የኢትዮጵያንና መሰል የአፍሪካ ሀገራትን ምርትና ምርታማነት ለማሻሻል፣ የተስተካከለ የአየር ንብረት እንዲሁም ዘላቂ ልማት እንዲኖራቸው በማለም እ.ኤ.አ በ2015 በአሜሪካ ኒውዮርክ የተቀረጸና በ2030 የሚጠናቀቅ አጀንዳ ነው፡፡ ምርምር ለማከናወን የሚገጥሙ ሀገራዊ የበጀት ተግዳሮቶችን ለመፍታት ዓለም አቀፋዊ የምርምር ተቋማት አጋርነት መፍጠር የሚያስችል ዕውቀትና ክሂሎት ለማስጨበጥ ሥልጠናው መዘጋጀቱን ዲኑ ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የግራንትና ትብብር ፕሮጀክት ማኔጅመንት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶማስ ቶሮራ የፕሮጀክት አጻጻፍን አስመልክተው በሰጡት ገለጻ የሚዘጋጁ ፕሮፖዛሎች ግልጽና የ2030 ዘላቂ የልማት ግቦችን ትኩረት በማድረግ በሴቶች፣ ሕፃናት፣ አርብቶ አደሮችና መሰል ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ቶማስ ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት አንዷ መሆኗ፣ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አንጋፋ የትምህርትና የምርምር ተቋም መሆኑ እንዲሁም ነባርና ብቁ ተመራማሪዎች መኖራቸው በተቋሙ የሚከናወኑ የምርምር ፕሮጀክቶች የተቀባይነት ዕድላቸውን ከፍተኛ ያደርገዋል፡፡

በእንስሳት ሳይንስ ት/ክፍል መምህርና ተመራማሪ ፕ/ር ይስሃቅ ከቸሮ በበኩላቸው ዓለም አቀፍ የምርምር ፕሮጀክቶችን ለማዘጋጀት የ2030 ዘላቂ የልማት ግቦችንና የልማት መርሆዎችን መጥቀስ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ተወዳዳሪነትን በሚጠይቀው ዓለም አብሮ መሥራትና ተያይዞ ማደግ ወቅቱ የሚፈልገው ጉዳይ መሆኑንም አውስተዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ምርምሮች በ2030 የልማት አጀንዳ የልማት ግቦች በሆኑት ድህነትን ማጥፋት፣ ጤናማነት፣ ጥራት ያለው ትምህርትና የጾታ እኩልነት እንዲሁም ብልጽግና፣ ሰላም፣ አጋርነትና የመሳሰሉ የዘላቂ ልማት መርሆዎች ላይ ትኩረት ያደረጉ ሊሆኑ እንደሚገባ በሥልጠናው ተጠቁሟል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት