አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለ26 ጊዜ በኢትዮጵያ ለ14 ጊዜ የተከበረውን የመቻቻልና የአብሮነት ቀን ‹‹ብዝኃነትን መኖር›› በሚል መሪ ቃል ታኅሣሥ 25/2016 ዓ/ም አክብሯል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ በዋናው ግቢ፣ የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በዓባያ ካምፓስ እና በም/ፕሬዝደንት ማዕረግ የሳውላ ካምፓስ ኃላፊ  አቶ ገብረመድኅን ጫሜኖ በሳውላ ካምፓስ መድረኩን ሲመሩ ባለንበት ዘመን ብዝኃነትን የመኖር መርህ በዓለም ላይ ከሚነሱ አስፈላጊ አጀንዳዎች ውስጥ አንዱና ዋነኛው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በመድረኮቹ እንደተገለጸው ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ተከትሎ ላለፉት በርካታ ዓመታት ዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ በሰላም አብሮ በመኖር መርህ ላይ በትኩረት ሲሠራ የቆየ ሲሆን በሰብአዊ መብቶች፣ እኩልነት፣ መድልኦንና ማግለልን መቀነስ፣ አካታችነት፣ መቻቻልና በሰላም ግንባታ የተሠሩ ሥራዎች ለአብነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ስምምነት መሠረት ብዝኃነትን መኖር ማለት ልዩነቶችን ተቀብሎ አብሮ በሰላም መኖር ማለት ሲሆን የሌላውን ባህል፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ አስተሳሰብ፣ ወግና ሥርዓት ተቀብሎ አንዱ ሌላውን ሳይንቅ የጋራ እሴት መገለጫ የሆነውን ሰላምን በማስቀደም ተቻችሎና ተደማምጦ መኖርን ያካትታል፡፡

እንደ ኃላፊዎቹ ገለጻ በተለይም ከሰማንያ በላይ ብሄሮችና ብሄረሰቦች፣ ቋንቋዎች፣ ሃይማኖቶችና በርካታ የፖለቲካ አስተሳሰቦች ባሉባት ኢትዮጵያ በአብሮነት መኖር አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሀገራችን በርካታ ግጭቶችና አለመግባባቶችን እያስተናገደች መሆኑ ብዝኃነትን መኖር ላይ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እንደሚጠበቁብን ያሳያል፡፡ በዓሉ ይህንን መሠረት በማድረግ የሚከበር መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊዎቹ በኢትዮጵያ ያለውን ብዝኃነት ማጉላትና ባለፉት ዓመታት በኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ መስኮች በአብሮነት የዘለቁ እሴቶችን ማንጸባረቅ ዋና ዓላማው ነው፡፡ ይህም ውበታችንን ከማጉላት አልፎ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ ብሎም ብልጽግናን ለማምጣት ጉልህ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ተቋሙ የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ በአብሮነት መኖርና በሰላም ግንባታ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን፣ ምርምሮችና ጥናቶችን፣ ሴሚናሮችና ወርክሾፓችን እንዲሁም የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት በዘርፉ መጠነ ሰፊ ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባም ተመላክቷል፡፡

በዕለቱ  በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የኪነጥበብ ክበብ አባላት በዓሉን የተመለከቱ ሥነ ግጥም፣ መነባንብ እና ሙዚቃዎች የቀረቡ ሲሆን ከአዲስ አበባ በቀጥታ ስርጭት ሊተላለፍ የታሰበው መልእክት በሥፍራው በገጠማቸው የቴክኒክ ችግር ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት