በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ቅጥር ግቢ ውስጥ እየተከናወነ በሚገኘው የከተማ ግብርና ሥራ ውብና ማራኪ አካባቢ ከመፍጠር ባሻገር ሙዝ፣ ፓፓያ፣ ግሽጣና ሌሎች ፍራፍሬዎች ለሽያጭ በማቅረብ ለተቋሙ ተጨማሪ ገቢ እያስገኙ መሆኑ ተገለጸ፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ጠቅላላ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዓለማየሁ ወልዴ የከተማ ግብርና ሥራው በ2014 ዓ/ም የተጀመረ መሆኑን አስታውሰው አሁን ላይ የጉድጓድ ውኃ እንዲሁም ከመምህራን መኖሪያ የሚወጣን ፍሳሽ በማከምና ጥቅም ላይ በማዋል ከሦስት ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ የፍራፍሬ ዝርያዎች መሸፈን ተችሏል ብለዋል፡፡ የለማው ሥፍራ ከዚህ ቀደም ምንም ዓይነት አገልግሎት የማይሰጥ፣ በቁጥቋጦ የተሞላና ለዕይታ የማይማርክ እንደነበረ የተናገሩት ዳይሬክተሩ አሁን ላይ በተሠራው ልማት ቦታውን ምቹና ውብ ማድረግ ከመቻሉ ባሻገር በየጊዜው ለጽዳትና ምንጣሮ ሥራ የሚወጣውን ወጪ ማስቀረቱን ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ዓለማየሁ በተወሰነ ደረጃ ለምርት የደረሱ የግብርና ውጤቶችን ለግቢው ማኅበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ እንዲሁም በሌሎች አማራጮች በሚደረግ ሽያጭ ለዩኒቨርሲቲው ገቢ ማስገባት የተቻለ ሲሆን ለአብነትም በ2016 በጀት ዓመት እስከ 2 ሩብ ዓመት ድረስ ከ421,000 (አራት መቶ ሃያ አንድ ሺህ) ብር በላይ ማግኘት ተችሏል፡፡ በዋናው ግቢም ሆነ በሌሎች ካምፓሶች ውስጥ በመሰል ሁኔታ መልማት የሚችሉ ቦታዎች መኖራቸውን የተናገሩት ዳይሬክተሩ በትንሽ ወጪና ያለንን የውስጥ አቅም በመጠቀም ብቻ ግቢዎችን ማልማት የሚቻል በመሆኑ ሌሎች ካምፓሶችም ተሞክሮ ወስደው እንዲሠሩ ጠቁመዋል፡፡ ቦታውን የማልማት ሥራ እዚህ ደረጃ እንዲደረስ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ድጋፍ፣ ክትትልና የሞራል ማበረታቻ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው የገለጹት አቶ ዓለማየሁ በቀጣይ ጊዜያትም ሥራውን የማስፋትና ይበልጥ አጠናክሮ የመቀጠል ዕቅድና ከፍተኛ ፍላጎት ያለ በመሆኑ አስፈላጊው ትብብርና ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች አገልግሎት አስተባባሪነት በዋናው ግቢ በሚገኙ የተማሪ መመገቢያ ካፍቴሪያዎች አካባቢ የሚገኙ ክፍት ቦታዎች በፍራፍሬና ሌሎች ተክሎች እየለሙ መሆኑን የተማሪዎች አገልግሎት ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ካፒታ ዋልጬ ገልጸዋል፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ የለማው ሥፍራ ከዚህ ቀደም በቆሻሻና በቁጥቋጦ የተሞላ የነበረ ሲሆን ያለምንም ተጨማሪ ወጪ የምግብ ቤት ሠራተኞችን በማሳተፍ አንድ ሄክታር የሚሆን ቦታን በሙዝ፣ ፓፓያ፣ አቮካዶና ቡና ተክሎች መሸፈን ተችሏል፡፡

ከፍራፍሬዎቹ ዋነኛው የሙዝ ተክል ነው ያሉት አቶ ካፒታ አሁን ላይ ተክሉ ለምርት የደረሰ በመሆኑ በበዓላት ወቅት ለተማሪዎች እየቀረበ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ የሙዝ ምርቱን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ለሽያጭ ለማቅረብ እየተሠራ ሲሆን በቅርቡ ለተቋሙ ገቢ ማስገኘት እንጀምራለን ብለዋል፡፡ የተከናወነው የልማት ሥራ የአካባቢውን ገጽታ ሙሉ በሙሉ የቀየረና ቦታውን ማራኪና ውብ ያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በቀጣይ ጊዜያትም መሰል ሥራዎችን ለማስፋት ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑንም አቶ ካፒታ አክለዋል፡፡

በሌላ በኩል በአርባ ምንጭ ውኃ ቴክኖሎጂ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጠቅላላ አገልግሎት አስተባባሪት ተመሳሳይ የከተማ ግብርና ልማት ሥራ እየተከናወነ ሲሆን በዚህም ከሁለት ሄክታር በላይ በሆነ ቦታ ላይ ሙዝ፣ አፕል-ማንጎ፣ አቮካዶና ግሽጣ እየለማ መሆኑን የሁለቱ ኢንስቲትዩቶች ጠቅላላ አገልግሎት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታምሩ ካሳ ገልጸዋል፡፡ አቶ ታምሩ ሥራው እንደ ሀገር እየተከናወነ የሚገኘውን የአረንጓዴ አሻራ ሥራ አስመልክቶ የተጀመረ ሲሆን ከዚህ ቀደም ክፍት የነበሩ ቦታዎችን በማልማት የአካባቢውን ገጽታ መቀየር ተችሏል ብለዋል፡፡ በሁለት ሄክታር መሬት ላይ የተተከለው የሙዝ ምርት ለሽያጭ የደረሰ መሆኑን የገለጹት አቶ ታምሩ በቅርቡ ለገበያ በማቅረብ ለዩኒቨርሲቲው ገቢ ማስገኘት እንደሚጀምሩና በቀጣይም መሰል ባዶ ቦታዎችን በተመሳሳይ መልኩ የማልማት ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት