አርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ‹‹Emerging Digital Technologies for Improved Aquatic Ecosystem Services›› በሚል ርእስ ከስዊድን ሀገር ማልሞ ዩኒቨርሲቲ (Malmo University) ከመጡት ዶ/ር ፍሥሃ መኩሪያ ጋር ታኅሣሥ 25/2016 ዓ/ም   ሴሚናር አካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የኢንስቲትዩቱ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው የምርምር ዩኒቨርሲቲ መሆኑንና በቀጣይ ራስ ገዝ ለመሆን የጀመረውን ጉዞ ተከትሎ በምርምር፣ በፕሮጀክቶች፣ በማኅበረሰብ ጉድኝትና ተወዳዳሪ አማካሪ ድርጅቶችን በመመሥረት ከተለያዩ ድርጅቶች፣ ግለሰቦችና ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር እየሠራ ነው፡፡

ከስዊድን ሀገር ማልሞ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ዶ/ር ፍሥሃ መኩሪያ ‹‹ውኃ ለሁሉም፣ የውኃ ደኅንነት ለፕላኔቷ/Water4All – Water Security for the Planet/ የተሰኘውን የአውሮፓ ኅብረት ፕሮጀክት አስመልክቶ እንዲሁም ለውኃ ውስጥ ሥነ ምኅዳር አገልግሎት በሚውሉ የተሻሻሉና አዳዲስ ዲጂታል ቴክኖሎጂዎች ላይ ለኢንስቲትዩቱ መምህራንና ተማሪዎች ሴሚናሩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ በዚህም ውኃ ለሁሉምና የውኃ ውስጥ ሥነ ምኅዳር ግልጋሎቶችና ባህርያት ላይ ገለጻ መደረጉን የጠቆሙት ዶ/ር ፍሥሃ ንጹሕ ውኃን ለሁሉም ማኅበረሰብ ለማድረስ በሚያስችል መልኩ አዳዲስ ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ለውኃ አካላት ጥበቃ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን እና ፕሮጀክቱ ለውኃ አስተዳደር ጠቃሚና ዘላቂ መፍትሔዎችን ለመፍጠር ትልቅ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በኢንስቲትዩቱ የኮምፒውቲንግና ሶፍትዌር ምኅንድስና መምህር ዶ/ር መሐመድ አበበ እንደገለጹት ቴክኖሎጂን ለውኃ፣ ለግብርናና ሌሎች መስኮች መጠቀምን የሚያሳይ በመሆኑ ሴሚናሩ በአጠቃላይ ለሁሉም ፋከልቲዎች አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከሴሚናሩ ቴክኖሎጂን የት፣ እንዴትና በምን መልኩ መጠቀም እንዳለባቸው ጠቅለል ያለ መረጃ ማግኘታቸውንም ተናግረዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት