አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣንና ከጋሞ ዞን ቱሪዝም መምሪያ ጋር በመተባበር “የጋሞ ዱቡሻ እና የዱቡሻ ዎጋ˝ ሥርዓት የጥናትና ምርምር ማስጀመሪያ የማኅበረሰብ ንቅናቄ መድረክ ጥር 25/20/16 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የኢትዮትያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ም/ዳይሬክተር አቶ ኤልያስ ሽኩር ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የብዝሃ ባህል ሀገር ስትሆን ሕዝቦቿም የባህል ልዩነት ሳይገድባቸው ለዘመናት የማይዳሰሱ ቅርሶችን በጋራ ተንከባክቦውና ተከባብረው መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

"የዱቡሻ ዎጋ" ለጋሞ ማኅበረሰብ የማንነቱ መገለጫ፣ ለረጅም ዘመናት ሲተገብረውና ሕይወቱንና ዘላቂ ሰላሙን ሲያስጠብቅ የኖረበት፣ የጋሞ ማኅበረሰብ እርስ በራሱና ከሌሎች ብሔረሰቦች ጋር ተዋዶና ተዛምዶ የኖረበት ባህላዊ ዕሴቱ እንደሆነ አቶ ኤልያስ ተናግረዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2003 ዓ/ም በሀገራችን ኢትዮጵያ በወጣው የዩኔስኮ መመሪያ መሠረት አምስት የማይዳሰሱ ቅርሶች በዩኔስኮ/UNESCO/ መመዝገባቸውን የተናገሩት አቶ ኤልያስ በያዝነው ዓመትም የዱቡሻ ሥርዓትን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ በጋራ እንሠራለን ብለዋል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ፍሬሕይወት ዱባለ እንደገለጹት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሀገሪቱ መንግሥት ረጅም ዘመናት ላስቆጠሩ ቅርሶች ከፍተኛ ትኩረት በመስጠትና ከፍተኛ የሆነ መዋዕለ ንዋይ በመመደብ በዓለም እንዲታወቁ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ በዚህም መሠረት ሀገራችን አሥራ አንድ መካነ ቅርሶችንና  አምስት የማይዳሰሱ ባሕለዊ ቅርሶችን በዩኔስኮ ያስመዘገበች ሲሆን ከነዚህም መካከል በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙት  የኮንሶ እና የጌዲዮ መልክዓ ምድር እንዲሁም የታችኛው ኦሞ ሸለቆ ተጠቃሾች እንደሆኑ ወ/ሮ ፍሬሕይወት ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን በክልሉ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር የወላይታ ዘመን መለወጫ (ጊፋታ) በዓልን፣ የጋሞ ዱቡሻ እና የዱቡሻ ዎጋን እንዲሁም የደራሼ ፊላ ሙዚቃ ባህላዊ ክዋኔን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ከኢትያጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን እንዲሁም ከጋሞና ጋርዱላ ዞኖች ጋር በጋራ እየሠሩ መሆናቸውን ወ/ሮ ፍሬሕይወት አክለዋል፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም በጥናትና ምርምር የማኅበረሰቡን ዕውቀት ለማሸጋገር እያደረገ ላለው ጥረት አመሥግነዋል፡፡

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳር ተወካይ አቶ በርገኔ በቀለ በበኩላቸው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ካሉዋት ባሕላዊ ቅርሶች አንዱ የሆነው የጋሞ ዱቡሻ ዎጋ በዘላቂነት እንክብካቤ ተደርጎለት የሰው ልጅ ቅርስ ወካይ ሆኖ በዩኔስኮ እንዲመዘገብና እንዲተዋወቅ በተለያዩ መድረኮች ኅብረተሰቡ ጥያቄ ማንሳቱን ተከትሎ በክልልና በዞን ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር ለተነሱ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ታስቦ መድረኩ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አቶ በርገኔ አክለውም ባህላዊ ቅርሱ በውስጡ ለዘመናት የካበተውን ዕውቀት፣ ጥበብ፣ ተሞክሮ እና ክሂሎት ከመያዙም ባሻገር የሕዝቦችን የሠላም ግንባታ የማስተዋወቅ ዕድሉም ከፍተኛ በመሆኑ ባሕላዊ ቅርሱ ወይም የዱቡሻ ዎጋ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ  ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት ሀገራችን በሀገር በቀል መልካም ዕሴቶችና ዕውቀቶች ላይ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች መሆኑን ገልጸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ለማበልጸግ በሥርዓተ ትምህርት አካተው በመማር ማስተማርና በምርምር በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

የጋሞ ዱቡሻ በሀገራችን ካሉ የማኅበረሰቡን ሠላም፣ ፍቅር፣ መተሳሰብንና መከባበርን ከሚያጎናጽፉ እንዲሁም እጅግ ጎልተው ከሚታወቁ ባሕላዊ ዕሴቶች ውስጥ የሚመደብ ብሎም አሁን በሀገራችን ከሚታየው ነባራዊ ሁኔታዎች አንጻር እጅግ ተፈላጊ እንደሆነም ፕሬዝደንቱ አክለው ተናግረዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው የባህልና ቋንቋ ጥናት ተቋምም ከጋሞ ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ጋር በመተባባር ጥናቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ዶ/ር ዳምጠው አሳስበዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በበኩላቸው ሀገራችን በርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ቋንቋዎችና ባሕሎች የሚገኙባትና ብዝኃነት የሚንጸባረቅባት ስትሆን እስከአሁን ካስመዘገበቻቸው ቅርሶች በላይ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች አሏት ብለዋል፡፡ ይህንን በመገንዘብ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ከኢትያጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም  ከጋሞ እና ጋርዱላ ዞኖች ቱሪዝም መምሪያዎች ጋር የአራትዮሽ የምርምር ትብብር በመመሥረትና ሀብትን በመጋራት የምርምር ሂደቱን በጥሩ ሁኔታ እያስኬዱ መሆኑን ተ/ፕ በኃይሉ ጠቁመዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የባሕልና  ቋንቋ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ዶ/ር ሰኢድ አሕመድ በበኩላቸው ተቋማችን የጋሞ ዱቡሻ ዎጋን እና የዴራሼ ፊላ የሙዚቃ  ክዋኔን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ያመነጨው ሃሳብ ተቀባይነትን በማግኘቱ ከሁለቱ ዞኖች ጋር ቅርሶቹን ለማስመዝገብ የማኅበረሰብ ንቅናቄ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ በሁለቱ ዞኖችና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኙ ሌሎች ዞኖች ያሉ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶችን በጥናትና ምርምር በመለየት ለዓለም ለማስተዋወቅና በዩኔስኮ ለማስመዝገብ እንደሚሠራም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የቋንቋና ሥነ-ጹሑፍ ትምህርት ክፍል መምህር እና የዱቡሻ ዎጋ ጥናት ቡድን አባል ዶ/ር ተመስገን ምንዋጋው “የዱቡሻ እና  የዱቡሻ ዎጋ  በጋሞ ማኅበረሰብ” በሚል የውይይት መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን ዓላማውም  በጋሞ ዞን በተለያዩ ወረዳዎችና ቀበሌያት ያሉትን  የ"ዱቡሻ ዎጋ" መከወኛ እንዲሁም የማኅበረሰቡን ባሕል፣ ዕሴት፣ እምነትንና ማንነትን በግልጽ ማመላከት የሚችሉ ቦታዎችን መለየትና በዩኔስኮ ማስመዝገብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም “የዱቡሻ ጥናት የጋሞ ዎጋ ምንነት፣ ፋይዳዊና አሁናዊ ሁኔታዎችና የገጠሙ ተግዳሮቶች ላይ የተደረገ ዳሰሳ ጥናትና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች” በአቶ ወንድይፍራው ከተማ እና “የዱቡሻ ጥናት የጋሞ ዱቡሻ ዎጋ አከባበር ሥርዓት” በጋሞኛ በአቶ ታሪኩ ኦይቾ የተዘጋጁ የውይይት መነሻ ሰነዶች ቀርበዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንትና ም/ፕሬዝደንቶችን ጨምሮ ከኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ፣ ከጋሞ ዞን ምክር ቤት፣ ከጋሞ ዞን ባሕል ቱሪዝምና ልማት መምሪያ የመጡ ኃላፊዎችና ዳይሬክተሮች እንዲሁም የጋሞ አባቶች ተገኝተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት