የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ለኤሌትሪካልና ኮምፕዩተር ኢንጂነሪንግ ፋከልቲ 4 ዓመት የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች በስትሪም መረጣ ዙሪያ መጋቢት 18/2016 ዓ/ም ገለጻ አድርጓል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በኢንስቲትዩቱ የኤሌክትሪካልና ኮምፕዩተር ኢንጂነሪንግ ፋከልቲ ዲን መ/ር ሳተናው ሳንዶ እንደገለጹት ተማሪዎች በፋከልቲው ውስጥ ከሚገኙ የኢንጂነሪንግ የትምህርት ዘርፎች ማለትም፡- ከ“Electronics”፣ “Electrical Power”፣ “Communication”፣ “Computer” እና “Control & Instrumentation” ኢንጂነሪንግ የትምህርት መስኮች መካከል በፍላጎታቸውና ባላቸው ዝንባሌ መሠረት ስፔሻላይዝ/Specialize/ የሚያደርጉበትን አንዱን የትምህርት መስክ/stream/ በመምረጥ በቀጣይ ሁለት ዓመታት ተምረው የሚመረቁ ይሆናል ብለዋል፡፡ ምርጫቸውንም ሲመርጡ ስትሪሞች ያስቀመጧቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት፣ በቆይታቸው የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡበትንና በቀጣይም ውጤታማ የሚያደርጋቸውን እንዲሁም የተለያዩ የሥራ አማራጮችን ሊያስገኝላቸው የሚችለውን የትምህርት መስክ በማስተዋል መምረጥ እንዳለባቸው ዲኑ አስገንዝበዋል፡፡

የኤሌክትሮኒክስና የኮምፕዩተር ኢንጂነሪንግ ትምህርት መስኮች ኃላፊ መ/ር አማኑኤል ዘማች በበኩላቸው በፋከልቲው የሚገኙት አምስቱም ስትሪሞች እርስ በርስ የሚመጋገቡ ሲሆን ከስፋታቸው አንጻር አንድ ተማሪ በአንዱ የትምህርት መስክ ብቻ ስፔሻላዝ ማድረግ ስላለበት የስትሪም ምርጫው እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎቹም የሚፈልጉትን ስትሪም ለማግኘት የ4 ዓመት አጠቃላይ አማካይ ውጤት (GPA)፣ የ4 ዓመት የ1 መንፈቀ ዓመት የጋራ ዋና ዋና የትምህርት ዓይነቶች /ኮርሶች/ የማጠቃለያ ፈተና ውጤት እንዲሁም የዩኒቨርሲቲውን የስትሪም መረጣ መመሪያ እና የስትሪሙን መመልመያ መስፈርት ከግንዛቤ  ውስጥ በማስገባት እንደሚካሄድ አሳውቀዋል፡፡

የ4 ዓመት የኤሌክትሪካልና ኮምፕዩተር ኢንጂነሪንግ ተማሪ አሥራት ባልቻ በሰጠው አስተያየት የስትሪም መረጣውን አስመልክቶ የተደረገው ገለጻ በአራት ዓመታት የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የተሻለ ዝንባሌ ያሳዩበትንና በቀጣይ ስኬታማ እንዲሆኑ የሚያስችላቸውን የሥራ መስክ አሁን ላይ ሆነው በፍላጎታቸው እንዲመርጡና እንዲወስኑ የሚረዳቸው መሆኑን ተናግሮዋል፡፡

በገለጻው የአምስቱም ስትሪሞች ኃላፊዎች ተገኝተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት