የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ፣ ግብርና ሳይንስ እና ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጆች በመተባበር 10ውን ሳይንስ ለዘላቂ ልማት ዐውደ ጥናት መጋቢት 21/2016 ዓ/ም አካሂደዋል፡፡ በዐውደ ጥናቱ ከተለያዩ የሀገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ ተመራማሪዎች የተሳተፉ ሲሆን 18 ጥናታዊ ጽሑፎችም ቀርበዋል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንትና የፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ እንደገለጹት ዐውደ ጥናቱ ከተለያዩ የሙያ ዘርፎች የተወጣጡ ተመራማሪዎችና ባለሙያዎች የተሳተፉበትና በርካታ የዕውቀት ሽግግር የተካሄደበት ነው፡፡ የመማር ማስተማር ሥራችን በጥናትና ምርምር የታገዘና ችግር ፈቺ የሆነ ስልትን የተከተለ ሊሆን ይገባል ያሉት ዶ/ር ዓለማየሁ መምህራንና ተመራማሪዎች በዚህ መርሕ ላይ ተመሥርተው ተግባራቸውን ሊከውኑ እንደሚገባና ጥራትና ብቃት ያላቸው ምሩቃንና ምርምር እንዲኖር የክትትልና የቁጥጥር ሥርዓት፣ የአሠራር ማዕቀፍ፣ የግብዓት አቅርቦት እንዲሁም ጥራት ያለው አመራርና አስተዳደር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በበኩላቸው ሳይንስ የማኅበረሰቡን አጠቃላይ ችግር የምናውቅበትና መፍትሔ የምናፈላልግበት መንገድ ከመሆኑም በላይ በተመራማሪውና በተቋማት እንዲሁም በኅብረተሰቡ መካከል ያለውን መለያየት የሚያገናኝ ድልድይ ነው ብለዋል፡፡ ስለሆነም ሳይንስን ዘላቂ ለማድረግ የራሳችንን፣ የባለሙያዎቻችንንና የተመራማሪዎቻችንን አቅም፣ ዕውቀትና ሃሳብ አሰባስበን ወደ ተግባር በመለወጥ ችግሮቻችንን መፍታት መለማመድ እንዲሁም በራስ መቆም እንደሚገባ ም/ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡ ተመራማሪዎች ከተለያየ የትምህርት መስክ የመጡ በመሆናቸው በጋራ ስለዘላቂነት ማሰብ እንዳለባቸው ብሎም ሳይንስን ወደ ፊት ለመግፋትና ወደ ዘላቂነት ለማሻገር ሌሎች ሰዎችን ማዳመጥና ጠቃሚ ሃሳቦችን መቀበል እንደሚያስፈልግ ም/ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡ ዐውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች ያላቸውን ልምድ በማካፈል ለዘላቂ ትብብርና ለምርምር የሚሆኑ ዕውቀቶችን የሚለዋወጡበትና ሙያዊ ትስስር የሚፈጠርበት እንደሆነም ተ/ፕ በኃይሉ አመላክተዋል፡፡

የምርምር ዳይሬክቶሬት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም እንደገለጹት የዐውደ ጥናቱ ዓላማ በአሁኑ ወቅት እየተሠሩ ያሉ ምርምሮች ላይ የተለያዩ ተመራማሪዎችን በማገናኘት ሃሳብ እንዲለዋወጡና የዕውቀት ግብይት እንዲካሄድ ማስቻል ነው፡፡ ይህም በቀጣይ የተሻሉ የእርስ በእርስ የትብብር መንገዶችን ለመፍጠር ይረዳል ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማክሮ ባዮሎጂ መምህር ፕ/ር ፋሲል አሰፋ ‹‹ሳይንስ ለዘላቂ ልማትና እድገት›› በሚል ርእስ የዕለቱን ቁልፍ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን ሳይንስ ችግር ፈቺ ቢሆንም ግኝቱ በቴክኖሎጂ ካልተደገፈና ወደ ኅብረተሰቡ ካልወረደ የትም መድረስ እንደማይችል ጠቁመዋል፡፡ እንደ ፕ/ር ፋሲል ገለጻ የተገኙ ግኝቶች ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ሼልፍ ላይ እንዳይቀመጡ የፖለቲካ ቁርጠኝነት፣ በጀት እንዲሁም የዩኒቨርሲቲና ኢንደስትሪ ግንኙነት ያስፈልጋል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የራሳቸውን ገቢ ማስገኛ ዘዴዎች ፈጥረው ገቢ ለማግኘትና በሂደት ራሳቸውን ለመቻል ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸው ፕ/ር ፋሲል ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ዘላቂ ልማትን ለማምጣት ያሉንን ምርምሮች በመለየትና በእነርሱ ላይ በመሥራት ማጠናከር፣ በኢኮቱሪዝም፣ በሙዝና በእንሰት ምርምር ዙሪያ ያሉንን ግኝቶች ወደ ቴክኖሎጂ በማሸጋገር በሂደት ከተረጂነት ለመውጣት ሳይንስን ተደግፎ ስትራቴጂክ በሆነ መንገድ መሥራት እንደሚያስፈልግ ፕሮፌሰሩ ጠቁመዋል፡፡

ሌላኛው የቁልፍ መልእክት አቅራቢ ‹‹The Task Force for Global Health›› በተሰኘ ዓለም አቀፍ ድርጅት የአፍሪካ ሪጅናል ዳይሬክተር ዶ/ር ተሾመ ገብሬ የዘላቂ ልማት ምንነትንና ሳይንስ ለዘላቂ ልማት የሚኖረው አስተዋጽኦ ላይ ያቀረቡ ሲሆን የሚሠሩ ምርምሮች የአካባቢውን ኅብረተሰብ ዘላቂ የምግብ ዋስትና ሊያረጋግጡ የሚችሉ እንዲሆኑ እንዲሁም ዘላቂ ልማት ላይ የሚያሳድሩት በጎ ተጽዕኖ ጎልቶ ሊታይ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ለመድኃኒትነት የሚውሉ ዕፅዋትን በማጥናት ረገድ የተጀመረው እንቅስቃሴ በሰፊው ተጠናክሮ መቀጠልና በብዛት በማምረት ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ የገቢ ምንጭ መፍጠር ያስፈልጋል ያሉት ዶ/ር ተሾመ ፕላስቲክ ነክ የሆኑ የሚወገዱ ቆሻሻዎች በአካባቢና በከብቶች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያስከትሉ በመሆናቸው ችግሩን ለሚመለከተው አካል ለማሳየት በደንብ ሊሠራ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ በአጠቃላይ ኅብረተሰባችንን በቀጥታ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ላይ ብናተኩር ኑሮን ለመለወጥና ለማሻሻል ይረዳልም ብለዋል፡፡  

ዶ/ር ተሾመ በሀገራችን የትምህርት ተቋማት ውስጥ ምርምሮች በብዛት እንደሚካሄዱና በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተወስነው ከመቅረታቸውም ባሻገር አዲስ ነገር ይዘው ከመምጣት ይልቅ ድግግሞሽ እየበዛባቸው በመሆኑ ምርምሮች ኅብረተሰቡ ላይ በጎ ተጽዕኖ የሚፈጥሩና ኑሮንና አካባቢን ሊቀይሩ የሚችሉ እንዲሆኑ ማድረግ የወደፊት የትምህርት ፖሊሲ አቅጣጫ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ የእንስሳት ሳይንስ ት/ክፍል መምህርና ተመራማሪ ፕ/ር ይስሃቅ ከቸሮ በእንስሳት ሥነ ምግብ ላይ የማዕድናት እጥረት ተጽዕኖን አስመልክተው ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን ለእንስሳት አስፈላጊ በሆኑ 20 ንጥረ ነገሮች ላይ ጥናቱ ትኩረት ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡ የጥናቱ ዓላማ የእንስሳትን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ምቹ ሁኔታዎችን በምርምር ማግኘት ሲሆን እንስሳት በሕይወት እንዲኖሩ ከሚያገለግሉ ንጥረ ነገሮች ውስጥ የሆኑት ማዕድናት እጥረት ሲኖር እንስሳቱ እንደማይራቡና ወተት እንደማይሰጡ ብሎም ሌሎች ችግሮችን እንደሚፈጥር በጥናታቸው መረጋገጡን ፕ/ር ይስሃቅ አመላክተዋል፡፡

ከሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ተመራማሪ ሙስጠፋ ባቲ የምርምር ሥራቸውን ሲያቀርቡ የአየር ንብረት ስማርት የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማላመድ/Climate Smart Agricultural Technologies Adoption/ አገልግሎት ላይ ማዋል በአርሲ ዞን የስንዴ አምራች አርሶ አደሮች የምግብ ዋስትና ደኅንነት ላይ አዎንታዊና ወሳኝ ተጽዕኖ ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ የሚቋቋሙ ሰብሎችን ማምረት ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ይፈልጋል ያሉት ተመራማሪው ቴክኖሎጂዎቹ የሰብሉን ምርታማነት በዘላቂነት የሚያሳድጉ፣ የበሽታ ተጋላጭነትን የሚቀንሱና የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅምን የሚጨምሩ ናቸው ብለዋል፡፡ ተመራማሪው ቴክኖሎጂዎቹ ለምግብ ዋስትና ያላቸው አስተዋጽኦ አዎንታዊ ስለሆነ ለአካባቢው አነስተኛ የስንዴ አምራች አርሶ አደሮች ተደራሽ እንዲሆኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት