አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አሜሪካን ሀገር ከሚገኘው አላባስተር ኢንተርናሽናል/Alabaster International/ የተሰኘ ግብረ ሠናይ ድርጅት ጋር በመተባበር ከጨንቻ ዙሪያ ወረዳ ዶርዜ ሆሎኦና ሃይዞ ለተወጣጡ 18 ሴት ወጣቶችና እናቶች ከእንሰት ቃጫ እሴት የተጨመረባቸውና ቱሪስትን ማዕከል ያደረጉ ጌጣጌጦችንና ሌሎች ቁሳቁሶችን ማምረት የሚያስችል ሥልጠና ከመጋቢት 9/2016 ዓ/ም ጀምሮ ለ15 ቀናት ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ እንደገለጹት ሥልጠናው ከቃጫ ከተለመዱ ምርቶች ባሻገር እሴት የተጨመረባቸው የተለያዩ ምርቶችን በማምረት ማኅበረሰቡን ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከእንሰት አኳያ የሚሠራቸው ሥራዎች በዋናነት ሴቶችን ያማከሉና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን የገለጹት ም/ፕሬዝደንቱ ይህም ለዘመናት በእንሰት ማምረት ሂደት ውስጥ የተጎዱትን ሴቶች የመካስና የትሩፋቱ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ የማስቻል ግብን የያዘ ነው፡፡ ከቃጫ ጋር በተያያዘ ከዞን ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ መምሪያና ከሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የገበያ ትስስር መፍጠር ላይ በትብብር እንደሚሠራም ም/ፕሬዝደንቱ አውስተዋል፡፡

የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፍ በኩል ከእንሰት ተክል ጋር ተያይዘው በዩኒቨርሲቲው የበለጸጉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማኅበረሰቡ ማዳረስ ላይ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የእንሰት ምርታማነትን ለመጨመር በማለም ችግኝ የማፍላት ሥራዎችን በስፋት እያከናወነ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አውስተዋል፡፡ ይህም ሥልጠና የዚሁ ሥራ አካል መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ተክሉ ከእንሰት ቃጫ ከገመድ ባለፈ ሠልጣኞቹ የተለያዩ ጌጣጌጦችን አምርተው የተሻለ ገቢ እንዲያገኙ ማድረግና ኑሯቸው ተሻሽሎ ማየት ከሥልጠናው የሚጠበቅ ውጤት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የእንሰት ፕሮጀክት አስተባባሪና የባዮቴክኖሎጂ ተመራማሪ ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ ከእንሰት ከሚገኙ ተረፈ ምርቶች መካከል አንዱ ቃጫ ቢሆንም የሚሸጥበት ዋጋ ዝቅተኛ በመሆኑ ማኅበረሰቡ የሚገባውን ያህል ጥቅም እያገኘ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በሥልጠናው ከዩኒቨርሲቲና ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ተመርቀው ሥራ ያላገኙ ወጣቶችና እናቶች የተሳተፉ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር አዲሱ ዶርዜና አካባቢው ከፍተኛ የሆነ የቱሪስት ፍሰት ያለበት አካባቢ እንደመሆኑ ለቱሪስቶች ለሽያጭ የሚቀርቡ የተለያዩ ጌጣጌጦችን ከቃጫ ማምረት የሚያስችል ክሂሎትና ዕወቅት ማስጨበጥ የሥልጠናው ዋነኛ ዓላማ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም መሰል ሥልጠና በሁለት ዙር ከጋሞና ወላይታ ዞኖች ለተወጣጡ ወጣቶችና እናቶች መሰጠቱን ያስታወሱት ዶ/ር አዲሱ 3ው ዙር ሥልጠና አሜሪካን ሀገር ከሚገኘው አላባስተር ኢንተርናሽናል  የተሰኘ ግብረ ሠናይ ድርጅት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የተሰጠ ነው ብለዋል፡፡

ዶ/ር አዲሱ በቀጣይ ጊዜያት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ሠልጣኞቹ በማኅበር ተደራጅተው ወደ ሥራ እንዲገቡ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ሠልጣኞቹ ያመረቱትን ምርት በቀላሉ ወደ ገበያ ይዘው እንዲቀርቡ አስፈላጊው ድጋፍና የገበያ ትስስር በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ እንደሚፈጠርላቸው አክለዋል፡፡

ወጣት ቤተልሔም ተስፋዬ በጋሞ ዞን የዲታ ወረዳ ነዋሪ ስትሆን ከዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ በ2015 ዓ/ም ተመርቃለች፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም ከእንሰት ቃጫ እሴት የተጨመረባቸው ቁሳቁሶችን ማምረት ዙሪያ በሰጠው ሥልጠና ላይ መሳተፏን የምትገልጸው ወጣት ቤተልሔም በሥልጠናው የተሻለ አፈፃፀም በማስመዝገቧ አሁን ላይ በአሠልጣኝነት እየሠራች መሆኑን ተናግራለች፡፡ በዚህኛው ሥልጠና ከባለፈው ሥልጠና የተለዩ አዳዲስ ዲዛይኖችን በመሥራት የተሻሉ ምርቶችን ሠልጣኞቹ ማምረት መቻላቸውንና ሠልጣኞቹ የመጡበት አካባቢ ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰት ያለበት እንደመሆኑ በቶሎ ወደ ሥራ ቢገቡ በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቃሚ ይሆናሉ የሚል እምነት እንዳላትም ተናግራለች፡፡

ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በጋርመንት ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪ የ2008 ምሩቅ የሆነችው ሠልጣኝ ሙሉነሽ ጦና በበኩሏ በሥልጠናው ሂደት ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ ከቃጫ በእጅጉ ውብ የሆኑ ጌጣጌጦችና የቤት ውስጥ ዕቃዎችን መሥራት መቻሏን ተናግራለች፡፡ ሥልጠናው ጌጣጌጦችን ከማምረት ባሻገር በቀጣይ በዘርፉ ለሚሠሯቸው ሥራዎች ከፍተኛ ተነሳሽነትን የፈጠረ በመሆኑ በቀጣይ በማኅበር በመደራጀት በዘርፉ ለመሰማራትና ተጠቃሚ ለመሆን ከሌሎች ሠልጣኞች ጋር መስማማቷንም ሠልጣኟ ተናግራለች፡፡ ሥልናውን ላመቻቹ አካላትና ለአሠልጣኞች እንዲሁም ለሥልጠናው አስተባባሪዎች ልባዊ ምስጋና አቅርባለች፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት