የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ከጋሞ ዞን ቴክኒክና ሙያ መምሪያ ጋር በመተባበር ለቴክኒክና ሙያ ተቋማት መምህራን ‹‹Advance Solid Work››፣ ‹‹Basic Solid Work›› እና ‹‹ArchiCAD›› በተሰኙ ሶፍትዌሮች ዙሪያ ከመጋቢት 15-19/2016 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ በሥልጠናው ከጋሞ፣ ጎፋ፣ ኮንሶና ደቡብ ኦሞ ዞኖች የተወጣጡ መምህራን ተሳትፈዋል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ እንደገለጹት ሥልጠናው  የቴክኒክና ሙያ መምህራንን የቴክኖሎጂ አቅም በመገንባት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠር ወደ ማኅበረሰቡ ማሸጋገር እንዲችሉ በየዓመቱ የሚዘጋጅ ነው፡፡ ሠልጣኞች በሥልጠናው ያገኙትን አዳዲስ ክሂሎትና ዕውቀት በመጠቀም ለተማሪዎቻቸው በተግባር ሠርተው ማሳየት እንደሚጠበቅባቸውም ዶ/ር ቶሌራ አውስተዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ፖሊ ቴክኒክና ሳታላይት ኢንስቲትዩት ም/ዲን አቶ ወርቅነህ ኃ/ሚካኤል ሥልጠናውን የሚወስዱት በዋናነት በቀጥታ ከሙያው ጋር ግንኙነት ያላቸው ባለሙያዎች ሲሆኑ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ትግበራ ክፍተታቸውን ለመሙላት ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመተባበር የሚሰጥ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ነው ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሜካኒካል ምኅንድስና ፋከልቲ መምህርና አሠልጣኝ አቶ ዮሐንስ ሰለሞን ሠልጣኞች ሃሳባቸውን ወደ ተግባር እንዲቀይሩ የሶፍትዌሮቹ ክሂሎት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው በሥልጠናው በሶፍትዌሮቹ አጠቃቀም ዙሪያ መሠረታዊ ዕውቀትና ክሂሎት እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ሌላኛው የፋከልቲው መምህርና አሠልጣኝ ጥላሁን ካሣ በበኩላቸው ሥልጠናው ሶፍትዌሮችን በተግባር እንዲጠቀሙ መሠረታዊ ዕውቀት የሚያስጨብጥ ሲሆን የሕንፃዎችን በቀላሉ ዲዛይን መሥራት እና ከመገንባቱ በፊት ምን ይመስላል የሚለውን መለየት የሚቻልበት መንገድ ላይ ሠልጣኞቹ የተግባር ክሂሎት እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ሥልጠናው በሶፍትዌሮቹ አጠቃቀም ላይ የሚስተዋለውን የክሂሎት ክፍተት ለመሙላት ትልቅ ሚና ስላለው መሰል ሥልጠናዎች ተጠናክረው አንዲቀጥሉ ሠልጣኞች ጠይቀዋል፡፡

በሥልጠናው መጨረሻ ለሠልጣኞች የምስክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት